በኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ስራ የገቡ ባለሃብቶች ምርቶቻቸውን ለገበያ እያቀረቡ ነው

99

ደብረ ብርሀን ጥቅምት 14 /2014 (ኢዜአ)-በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ የተሰማሩ ባለሀብቶች ለአፍሪካ አገራት የተሰጠውን ከቀረጥና ኮታ ነፃ ዕድል ሳይጠብቁ ባላቸው የገበያ አማራጭ ምርቶቻቸውን ለአውሮፓ አገራት እያቀረቡ መሆኑ ተገለጸ።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ የሺጥላ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንዳሉት በፓርኩ ውስጥ ያሉ ስምንት የማምረቻ ሼዶች ሙሉ በሙሉ ለውጭ ባለሃብቶች ተሸጋግረዋል።

በፓርኩ ገብተው ወደ ሥራ ከገቡት መካከል በስፔን ባለሃብት የተቋቋመው "ኢኬ የጨርቃጨርቅ ማምረቻ ፋብሪካ" አንዱ ሲሆን በራሱ የገበያ ትስስር ምርቶቹን ለአውሮፓ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

ፋብሪካው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ወደ ውጭ ከላካቸው የአልባሳት ምርቶች 2 ሚሊዮን 475 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለኢትዮጵያ ማስገኘቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለሀገር ውስጥ ተተኪ ምርቶችን እያቀረበ ያለው ''ፑርትማንት ብቅል ፋብሪካ'' በሩብ ዓመቱ 14 ሺህ ቶን ብቅል በማምረት ለሃገር ውስጥ ገበያ ማቅረቡን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ፋብሪካው ያቀረበው የብቅል ምርት ከውጪ ቢገዛ ሊወጣ የሚችለውን 14 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንዳስቻለ አመልክተዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የኤሌክትሪክ ሃይል፣ የስልክና የባንክ አገልግሎት እየተሰጠ ነው።

ይህን ተከትሎም በአካባቢው በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶች ፍላጎት በእጅጉ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በፓርኩ ወደ ሥራ የገቡ ፋብሪካዎች 1ሺህ 80 ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።

የኢኬ የጨርቃጨርቅ ማምረቻ ፋብሪካ የሽያጭ ባለሙያ ወይዘሪት እየሩሳሌም ምትኬ በበኩሏ ባለሀብቶቹ ቀረጥ ከፍለው በራሳቸው የገበያ መዳረሻ ምርታቸውን የሚያቀርቡበት አማራጭ ሰፊ መሆኑን  ገልጻለች።

ባለሀብቶቹ ከአግዋ የታክስ ማበረታቻ ዕድል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ተናግራለች።

"በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው የማምረት አቅሙን ከቀዳሚው ዓመት በአራት እጥፍ በማሳደግ ምርቱን ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል" ብላለች።

ከዚህ በፊት በቀን ከ1 ሺህ 200 ሹራቦችን የመሸመን አቅም ያለው ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት በቀን 4 ሺህ ሹራብ በመሸመን አቅሙን ማሳደጉን ጠቅሳለች።

ወይዘሪት እየሩሳሌም እንዳለቸው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 ፋብሪካው 200 ሺህ ሹራብ ለውጭ ገበያ የላከ ሲሆን በተያዘው የፈረንጆች ዓመትም 700 ሺህ ሹራብ ልኳል።

ከፋብሪካው ሠራተኞች መካከል አቶ ተመስገን ማስረሻ እንዳሉት በፋብሪካው ከተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ባለፈ የሙያ ክህሎት ስልጠና እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

የግንባታ ሥራው በ72 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተካሄደው የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሁለት ዓመት በፊት ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም