የህብረት ስራ ማህበራት መበራከት ለግብርና እድገት አስተዋጾ የላቀ መሆኑ ተመለከተ

83

ጭሮ ጥቅምት 14/2014(ኢዜአ) የህብረት ስራ ማህበራት መበራከት ለግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት አስተዋጾ የላቀ መሆኑ ተመለከተ ።
በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ግብርናን በማዘመን የምርት መጠንና ጥራትን ማሳደግ ዓላማ ያደረገ የምክክር መድረክ አካሂደዋል ።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ ከበደ በወቅቱ እንዳሉት የግብርና ህብረት ስራ ማህበራት መበራከታቸው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በግብርና መር ኢኮኖሚ የምትተዳደረውን ሀገራችንን አቅም ከፍ ማድረግ ያስችላል፡፡

በመንግስት ከሚቀርበው ግብዓት በተጨማሪ የህብረት ስራ ማህበራት ምርጥ ዘርን እያባዙ ለገበሬው  በማድረስ  የምርት መጠን እንዲጨምር  እያደረጉ ያለውን ጅማሮ ማበረታታት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

አርሶ አደሩ ስልጠናዎችን በመውሰድ ንቁ ተሳታፊነቱን በማጎልበት የሀገርንና የራሱን ኢኮኖሚ የማሳግ ግዴታውን እንዲወጣ ጠቁመዋል፡፡

ገበሬው የዝናብ ወቅትን ብቻ ጠብቆ ከማምረትና ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ከመምራት አልፎ መስኖን በመጠቀም ግብርናውን አሻሽሎ ከሀገሩ ተርፎ ወደ አለም ተወዳዳሪ አምራችነት መሸጋገር እንደሚገባው  አስተዳዳሪው አሳስበዋል፡፡

በዞኑ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አህመድ መሀመድ በበኩላቸው "አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም በማደራጀት ምርጥ ዘር፣ የሰብል እንክብካቤና የግብርና ዘዴ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት ሰፊ ስራ ተሰርቶ ውጤት ማሳየት ተችለዋል" ብለዋል፡፡

"በዚህም በአንድ ሔክታር የገበሬ ማሳ ስምንት ኩንታል ሲያመርት የነበረው አማካኝ የሰብል ምርትን ከ35 እስከ 50 ኩንታል በማድረስ የለውጥ መንገድ ተጀምሯል" ሲሉ ለአብነት ጠቅሰዋል ፡፡

አያይዘውም የግብርና ህብረት ስራ ማህበራቱ ገበሬውን በግብርና ግብአቶችና በገንዘብ ድጋፍ ከመርዳት ባሻገር የልጆቻቸውን የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላትና ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ሰፊ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ወይዘሮ መሪያ ኡመር የቡርቃ ጋሪቲ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር አባል ሲሆኑ በማህበር መደራጀታቸው ቀድሞ  ከነበረው በእጅጉ የተሻለ ምርትና ጥሩ ኑሮ እንዲመሩ ያስቻላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ምርጥ ዘርና እንደ ኮምባይነርና የመስኖ ውሃ መሳቢያ ሞተር የመሳሰሉ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን  በመጠቀም የሰብል ምርታማነታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም