በየደረጃው የሚገኙ የብአዴን አመራሮች የተሳተፉበት ኮንፈረንስ በባህር ዳር በመካሄድ ላይ ነው

68
ባህር ዳር ነሀሴ 12/2010 የብሔር አማራ ዴሚክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በሃገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስና የወቅቱን የአማራ ህዝብ ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዝ ኮንፈረንስ መጀመሩን የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የብአዴን አመራሮች እየተሳተፉ ነው። በጽህፈት ቤቱ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ''የለውጥ ሂደቱ በማንኛወም መንገድ እንዳይደናቀፍ ብአዴን በትኩረት ይሰራል'' ብለዋል። ''በውይይቱም ህዝቡ ለዘመናት ሲያደርገው በነበረው ያልተቆጠበ ግፊት የመጣው ለውጥ መሰረት እንዲኖረውና ዘላቂነቱ በሚረጋገጥበት ዙሪያ ጥልቅ ምክክር በማድረግ የመፍትሄ አቅጣጫ ይቀመጣል'' ብለዋል። እንዲሁም በህዝቡና በአመራሩ ጠንካራ ህብረት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ዜጎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ያለ ስጋት የሚኖሩበት ሁኔታ የማመቻቸት ሂደቶችም በስፋት የሚመከርባቸውና መግባባት ላይ የሚደረስባቸው ጉዳዮች ናቸው። እንደ ኃላፊው ገለጻ በምክክር መድረኩ በቀጣይ ለሚካሄደው የድርጅቱ ጉባኤ ለውሳኔ የሚያግዝ ግብአት የሚሰበሰብበት ነው፡፡ በተጨማሪም የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ያለፉት ሦስት ዓመታት የልማትና የመልካም አስተዳደር የእቅድ አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት አቶ ምግባሩ አስታውቀዋል። በኮንፈረንሱ የሚደረስባቸው የስምምነት አቅጣጫዎችም በቀጣይ እስከ ታች በመውረድ ከድርጅቱ አባላትና ከህዝቡ ጋር ውይይት እንደሚደረግባቸውም አብራርተዋል። ብአዴን ከችግሮቹ ተላቆ የአማራ ክልል ህዝብን መብትና ጥቅም ለማስከበርም ካለፉት ጊዜያት ትምህርት በመውሰድና ውስጡን በማጥራት በጠንካራ አመራር እንደሚሰራም አቶ ምግባሩ ተናግረዋል። ኮንፈረንሱ ዛሬ የተጀመረ ሲሆን በነገው እለትም በአጀንዳዎቹ ዙሪያ ምክክር በማድረግ የውስጥ የፖለቲካ አቅሙን በሚያጠናክረበት ዙሪያ ጠንካራ አቋም ይዞ እንደሚወጣም ይጠበቃል ሲሉ አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም