የአሸባሪውን ህወሓት ኢትዮጵያን የማፍረስ ከንቱ ምኞት በጋራ ክንድ እናመክናለን

84

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የአሸባሪውን ህወሓት "ኢትዮጵያን የማፍረስ ከንቱ ምኞት በጋራ ክንድ በመመከት እናመክናለን" ሲሉ የአፋር ክልል ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሎጊያ ከተማ የሃይማኖት አባት ሀጂ ኡስማን አብደላ መሀመድ እንደሚሉት፤ ለአፋር ህዝብ ስለ ኢትዮጵያዊነት መናገር ለቀባሪው እንደ ማርዳት ነው።

የአፋር ህዝብ መሪ የነበሩት ሱልጣን ሀንፍሬ አሊሚራህ "ይህቺን ሰንደቅ ዓላማ እንኳን እኛ ግመሎቻችን ያውቋታል" ብለው እንደነበር አስታውሰዋል።

የአፋር ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር መሆኑን ገልፀው፤ አሻባሪው ህወሓት "ኢትዮጵያን ለማፍረስ አፋርን እንደ መሰላል እጠቀማለሁ" ብሎ ማሰቡ ዋጋ እንዳስከፈለውና እንደሚያስከፍለውም ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት የጅቡቲን መስመር ለመያዝ ያደረገውን ሙከራ ህዝቡ ከመከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን መስዋዕትነት ከፍሎ በማክሸፍ በኢትዮጵያዊነቱ እንደማይደራደር ለጠላቶች በተግባር ማረጋገጡን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ህዝብ ሰላም በማሳጣት እረፍት የነሳውን አሸባሪ ቡድን ሁሉም ከጀግናው የአገር መከላከያ  ሰራዊት ጎን በመሰለፍ በጋራ ክንድ ሊመክት እንደሚገባ ነው አጽንኦት የሰጡት።

የሎጊያ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ከድጃ መሀሙድ በበኩላቸው፤ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የሚሰሩ ግለሰቦች በተለያየ መንገድ ሰላም ወዳዱን ህብረተሰብ ለማስጨነቅ ከኢኮኖሚ አሻጥር ጀምሮ የስነ ልቦና የበላይነት ለመውሰድ የሀሰት ወሬ እየነዙ በመሆኑ ስር ሳይሰድ "መንግስት በፍጥነት እርምጃ ሊወስድ ይገባል" ብለዋል።

ሁሉም በአንድነት ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፎ በጋራ ክንድ የሽብር ቡድኑን መመከት እንደሚገባውም አመልክተዋል።

አሸባሪው ህወሓት "በአፋር ክልል የፈጸመው ጥቃት ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮ አንዱ ማሳያ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ አሊ ቡተሊ ናቸው።

ይህ አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን የማፍረስ ፍላጎቱ እውን እንዳይሆን ሁሉም የሚጠበቅበትን ሀላፊነት መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

ሁሉም ነገር ሊኖር የሚችለው አገር ሲኖር ብቻ በመሆኑ አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ቡድኑን በጋራ መመከት ያስፈልጋል ብለዋል።

የሎጊያና ሰመራ አካባቢ የአገር ሽማግሌ አቶ ቡራባህ አሊ በበኩላቸው፤ ሴት ወንድ ትንሽ ትልቅ ሳይባል  ሁለም አገር አፍራሹን ቡድን ሊመክት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ያለውን አቅም ሁሉ አስተባብሮ አሸባሪውን ቡድን በጋራ ክንድ መመከት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም