በኢትዮጵያ 22 ሚሊዮን ዜጎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት እንዲወስዱ እየተሰራ ነው

59

ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 13/2014(ኢዜአ) የተያዘው ዓመት አጋማሽ ድረስ 22 ሚሊዮን ዜጎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት እንዲወስዱ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት አስታወቀ ፡፡

በኢትዮጵያ እስካሁን ከሶስት ሚሊዮን የሚበልጡ  ዜጎች ክትባት ወስደዋል።

የኢንስትቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከጥንቃቄ በተጨማሪ ክትባቱን መውሰድ ይገባል።

ኢንስትቲዩቱ ከዓለም ጤና ድርጅት፣ ከጤና ሚኒስቴርና ሌሎች አካላት ጋር በመተባበር እስከ ተያዘው ዓመት አጋማሽ 22 ሚሊዮን ዜጎችን በመከተብ 20 በመቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም "አስትራዜኒካ"፣" ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን"  እና "ሲኖ ፋርም " 10 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት በግዥና በዕርዳታ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን አስረድተዋል።

እስካሁንም ዕድሜን፣ ተጋላጭነትና የሥራ ሁኔታን ማዕከል በማድረግ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች መከተባቸውን አቶ አስቻለው አስታውቀዋል።

ክትባት መውሰድ ያለባቸው ዜጎች የዕድሜ ወሰን ወደ 18 ዓመት ዝቅ መደረጉንና የሥራ እንቅስቃሴያቸው ለቫይረሱ አጋላጭ የሆነባቸው ወጣቶች፣ የፀጥታ አካላት፣ መምህራንና አሽከርካሪዎች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።

''ክትባቱ በሁሉም የመንግሥት የጤና ተቋማት ተደራሽ እንዲሆን እየሰራን ነው'' ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለውጥኑ መሳካት ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ከመዘናጋት ወጥቶ ርቀቱንና ንጽህናውን በመጠበቅ እንዲሁም ከሰዎች ጋር ባለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወቅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በመጠቀም ራሱንና ማህበረሰቡን ከበሽታው እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት  የ 6 ሺህ 333 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ፤  361 ሺህ ሰዎች ደግሞ ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም