የኢትዮጵያ ሴት መምህራን ኮከስ ተመሰረተ

66

አርባምንጭ፤ ጥቅምት 13/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሴት መምህራን ኮከስ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተመሰረተ።

 ኮከሱን ለአራት ዓመታት  የሚመሩ አመራሮች ተመርጠዋል።

በኮከሱ ምስረታ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ  የሴቶችን አቅም፣ ዕውቀትና ጥበብ በመጠቀም ከአሁናዊ ችግሮች ለመሻገርና ለመጪው ትውልድ ስኬታማነት  ኮከሱ  አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የኮከሱን እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማጠናከር ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት  እንደሚሰራ ገልጸው፤ ሴት ምሁራን አርአያና ተተኪ የሚሆኑ ሴት አመራሮችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው፤ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለማስቆም ማህበሩ የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሴት መምህራን በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከኮከስ አመራር አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

ለዘመናት አብሮ የቆየው በሥርዓተ  ጾታ ዙሪያ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመለወጥ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ስራ አስፈጻሚና የስርዓተ ጾታ ክፍል ተጠሪ ወይዘሮ ደስታዬ ታደሰ ናቸው።

 ማህበረሰቡ ለሴቶች ያለውን የተዛባ አተያይ ለመለወጥ ኮከሱ ከኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጋር በቅንጅት መሰራት የሚበጅ  መሆኑን አመልክተዋል።

በአርባምንጭ የተመሰረተው የሴት መምህራን ኮከስ ለአራት ዓመታት የሚመሩ አመራሮቹን ተመርጠዋል።

በዚህም ፡-  

1/መምህርት ታደለች ጥርቀ ከደቡብ ክልል የኮከሱ ሰብሳቢ

2/መምህርት አፀደ ቱላ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ፀሐፊ

3/መምህርት ራቢያ ናስር ከኦሮሚያ ክልል ኘሮጀክት አስተባባሪ

4/መምህርት ደመቀች መኮንን ከአማራ ክልል አቅም ግንባታና ስልጠና አስተባባሪ

5/መምህርት ደብሪቱ ጌታቸው ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መረጃ አደረጃጀትና የህዝብ ግንኙነት ሥራ አመራር ሆነው ተሰይመዋል።

በኮከሱ ምስረታ ላይ  ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር  ስራ አስፈጻሚ አባላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም