በምዕራብ ሸዋ ዞን የሜታሮቢ ወረዳ አርሶ አደሮች የፀረ-አረም መድሃኒት እጥረት እንዳጋጠማቸው አስታወቁ

1549

አምቦ ነሀሴ 12/2010 በምዕራብ ሸዋ ዞን የሜታሮቢ ወረዳ አርሶ አደሮች  የፀረ-አረም መደሐኒት እጥረት እንዳጋጠማቸው አስታወቁ።

የወረዳው ህብረት ስራ ማህበራት ጽህፈት ቤት በበኩሉ የአርሶ አደሮቹ ቅሬታ ተገቢ መሆኑን ገልፆ ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የወረዳው አርሶ አደር ጫላ ኢጃራ በሰጡት አስተያየት በመኸር እርሻ የዘሩትን ሰብል ከአረም ለመከላከል የፀረ-አረም መደሐኒት እጥረት እንዳጋጠማቸው ገልፀዋል።

አምና በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ላለሙት ሰብል አንድ ሊትር የአረም መድሃኒት መጠቀማቸውን ገልጸው ዘንድሮ በዘር ለሸፈኑት ሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ግን ያገኙት መድኃኒት ሩብ ሊትር ብቻ በመሆኑ ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር ቤኩማ ቶለሳ እንዳሉትም እስካሁን የአረም መድሃኒት አለማግኘታቸው እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል ።

በኀብረት ስራ ማህበራት በኩል በ140 ብር  የሚቀርበው አንድ ሊትር ፀረ-አረም መደሃኒት በንግድ መደብር ከ400 ብር በላይ በመሆኑ ገዝተው ለመጠቀም መቸገራቸውን ገልጸዋል።

የአረም መድሐኒት እጥረቱ በመኸር እርሻ እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረሰ በመሆኑ መፍተሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል አርሶ አደሩ።

አርሶ አደር ከተማ ደምሴ በበኩላቸው በወረዳው ህብረት ስራ ማህበራት ፅህፈት ቤት የተሰራጫው የአረም መድሃኒት በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

እሳቸውም ከሚፈልጉት ሁለት ሊትር መድሃኒት ውስጥ እስካሁን ያገኙት ግማሽ ሊትር እንደማይሞላ ጠቅሰው በዚህ ረገድ ያለባቸው ችግር እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን የሜታሮቢ ወረዳ ህብረት ስራ ማህበራት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጉተማ ዲዳ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ”የአርሶ አደሮቹ ቅሬታ ተገቢ መሆኑን አምነው ስጋታቸውን ለማቃለል እየሰራን ነው” ብለዋል።

ጽህፈት ቤቱ ያሰራጨው 444 ሊትር ፀረ-አረም መደሐኒት አቅርቦቱና ፍላጎቱ ባለመጣጣሙ እጥረት ማጋጠሙን ገልጸዋል።

ችግሩን በማስመልከት ለዞኑ ማሳወቃቸውን ጠቅሰው ችግሩ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ እንደሚፈታ አስታውቀዋል ።