በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ43 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ሊለማ ነው

75

አሶሳ ፤ ጥቅምት 13/ 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 43 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ እንደሚለማ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ልማቱ የሚካሄደው በ2013/14 ምርት ዘመን የባከነውን ምርት ለማካካስ ነው።

ለልማቱ አነስተኛና  ዘመናዊ መስኖዎችን ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱንና ለዚህም 105 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን  በቢሮው የግብርና ኤክስቴንሽን ግብዓት አቅርቦት እና ስርጭት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ በጅጋ ፃፊዮ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ልማቱ በተለይ በመተከል የተገኘው አንጻራዊ ሠላም ዘላቂ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡

በልማቱ ከዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በመስኖ ከሚለማው መካከል በአብዛኛው አትክልት ቢሆንም በቆሎና ማሽላም እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

''ዕቅዱን ለማሳካት ከተለመደው ደካማና ቅንጅት ከጎደለው አሰራር ወጥተን ውጤታማ ለመሆን እየሠራን ነው'' ብለዋል፡፡

በ2013/2014 የመኸር ወቅት በክልሉ   ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለማልማት ታቅዶ 547 ሺህ ሄክታር ታርሶ መልማቱን አስታውሰዋል።

ለአፈጻጸሙ ማነስ በክልሉ በተለይ በመተከልና ካማሽ ዞኖች የጸጥታ ችግር ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አቶ በጅጋ አስረድተዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአሶሳ ዞን አርሶ አደሮች እንዳሉት፤ በ2013/14 የምርት ዘመን የግብርና ግብዓቶችን በመጠቀማቸውና ኩታ ገጠም አስተራረስ በመከተላቸው ሰብላቸው በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል።

በዞኑ ባምባሲ ወረዳ የሸቦራ ቀበሌ አርሶ አደር ሃሩን መሐመድ ፤ በ10 ሄክታር ላይ ባለሙት ማሽላና በርበሬ በሄክታር እስከ 200 ኩንታል አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

አርሶ አደር ተካ አስፋው በበኩላቸው፤ ምርጥ ዘርና ሌሎችን ግብዓቶችን ተጠቅመው ያለሙት በቆሎ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኩታ ገጠም አስተራረስ፣ የጋራ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራዎች በማከናወናቸው  ውጤታማ እንደሚሆኑ  አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም