በህዳሴው ግድብ ደን ምንጣሮ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ከ40 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኙ

94

አሶሳ፤ ጥቅምት 13 / 2014 (ኢዜአ) በህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የደን ምንጣሮ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ከ40 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸው ተገለጸ።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቴክኒክ እና ሙያ ስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ የስራ አፈጻጸሙን  በአሶሳ ገምግሟል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት  ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል፡፡

በሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት ደን ምንጣሮ ስራ በክልሉ የሚገኙ በ149 ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ከ1 ሺህ 300 በላይ ስራ አጦች ተሳታፊ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢንተርፕራዞቹ አባላት 2 ሺህ 736 ሄክታር መሬት የደን ምንጣሮ ስራ ማካሄዳቸውን አመልክተው፤  በዚህም ከ40 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጋ ብር በመቆጠብ ወደ ቋሚ ስራ መሸጋገራቸውን ዋና ዳይሬክተሩ  ጠቁመዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ፤  ሶስተኛውን የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት የሚካሄድበት ስፍራ የደን ምንጣሮ ስራ በመጪው ታህሳስ ወር  ለማስጀመር  ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በመጀመያው እና ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በተከናወነባቸው አካባቢዎች የተመነጠረው ደን እንዲቃጠል መደረጉን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውሰዋል፡፡

በተያዘው ዓመት የሚካሄደው የደን ምንጣሮ   የገቢ ምንጭ ለማድረግ ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የክልሉን ጸጥታ ወደ ቀደመ ሁኔታ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መሰተዳደሩ ፤ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ ለ32 ሺህ 700 ሰዎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ  ከ21 ሺህ 600 የሚበልጡ ሰዎች የእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም