የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ"ን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው

358

ሶዶ (ኢዜአ) ጥቅምት 12 ቀን 2014 የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ"ን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከሚያስችሉ ሥራዎች አብዛኞቹ መጠናቀቃቸውን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
 የዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አበሻ ሽርኮ ለኢዜአ እንዳሉት ጊፋታ የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ነው።

በዓሉ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ለማድረግ ከሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች አብዛኞቹ በአሁኑ ወቅት መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

"እስከሁንም የበዓሉ ባህላዊ ስነስርአት፣ በዕድሜና በጾታ የሚደረጉ ክዋኔዎችና ሌሎች የጊፋታን ስርዓት የሚያሳዩ ተግባራትን በጥናት በማስደገፍ የመሰነድ ስራ ተከናውነዋል" ብለዋል።

ጊፋታን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥያቄው ከቀረበ መቆየቱን የተናገሩት ዶክተር አበሻ በዓሉን በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ዋነኛ ጉዳዮችን የያዘ ፋይል ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በዓሉን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ከተጀመሩ ሥራዎች 70 በመቶ የሚሆኑት መጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።

ዶክተር አበሻ እንዳሉት በተያዘው የ2014 ዓ.ም የካቲት ወር ድረስ የፋይል ሥራው ተጠናቆ በመጋቢት ወር 2013 ዓም ለሚመለከተው አካል ይቀርባል።

በወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል፣ ታሪክና ቅርስ ሥራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ አዳነ አይዛ በበኩላቸው ከዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"በዓሉን በዩኔስኮ ማስመዝገብ ያለውን ሀገራዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታ በይበልጥ ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅ ተግባር እየተከናወነ ነው" ብለዋል።

በዓሉ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆንና በመጤ ባህል እንዳይበከል ለማድረግ ከወጣቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በወላይታ ዞን የሀገር ሽማግሌ አቶ አብርሃም ባቾሬ በበኩላቸው "የጊፋታ በዓል ከባህላዊና ታሪካዊ ይዘት ውጪ ሌላ ትርጉም የለውም" ብለዋል።

በዓሉ የወላይታን ብሔር ባህል፣ ታሪክና ቅርስ በዓለም እንዲተዋወቅ ከማድረግ ባሻገር ለቱሪዝም ፍሰት ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ የዘመን መለወጫ በዓሉን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ  በሚኖረውን ፋይዳ ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ በኮሚቴነት በመሳተፍ  የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጊፋታን በዩኔስኮ የማስመዝገቡ ሥራ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ከደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ባለድርሻዎች ጋር  በቅንጅት እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም