የቱሪዝም አገልግሎትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ዘርፉን ማነቃቃት ያስፈልጋል

95

ጥቅምት 11 / 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የቱሪዝም አገልግሎትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ዘርፉን ማነቃቃት እንደሚገባ ተጠቆመ።
የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ ሲፖዚየም አካሂዷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአገር ልማት ጥናት ኮሌጅ የቱሪዝም መምህር ዶክተር ተስፋዬ ዘለቀ፤ በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጹሁፍ አቅርበዋል።

በፅሁፋቸውም በኮቪድ-19 ምክንያት የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት እየተሰሩ ያሉ ተግባራት መጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ የለሙና እየለሙ ያሉ ግዙፍ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጨምሮ ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪስት መዳረሻ መስህቦች የማስተዋወቅ አካሄድ መዘመን እንዳለበትም ገልጸዋል።

ኮቪድ 19 በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያሳደረውን ጫና ለመቀነስ መዳረሻዎችን በስፋት ማስተዋወቅ፣ በቴክኖሎጂ መደገፍ፣ አማራጭ የቱሪዝም ምርት ሽያጮችን መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የቱሪዝም አገልግሎትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ዘርፉን ማነቃቃት ይገባል ብለዋል ዶክተር ተስፋዬ።

    በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተከሰተው የሰላም እጦት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተጨምሮ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ጫና ማሳደሩን ጠቅሰው አማራጭ መዳረሻዎች ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

አስጎብኝ ድርጅቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የቱሪስት ሃብቶችን አማራጭ አድረገው ማቅረብ እንደሚገባቸውም ነው የገለጹት።

በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና ብቃት ማረጋገጥ ዳሬክተር አምደማሪያም ማሞ፤ በከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን በተለያዩ አማራጮች ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

      የገርህን እወቅ ማህበር ሰብሳቢ ብርሃኑ ወዳጆ በበኩላቸው የሰላም ችግር ባለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች መሄድ ባይቻልም የኮቪድ-19 መመሪያዎችን በጠበቀ መንገድ በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስጎብኘት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

     የቱሪዝም ቀን በአለም ለ42ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም