በካሊፎርኒያ ሙዝየም የሚገኙ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለማስመለስ እየተሰራ ነው

108

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2014(ኢዜአ) በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ሙዝየም የሚገኙ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለማስመለስ እየተሰራ መሆኑን የብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የባህል፣ የታሪክና የማንነት መገለጫ የሆኑ በርካታ ቅርሶች በተለያዩ የአለም አገሮች እንደሚገኙ ይነገራል።

ቅርሶቹን ለማስመለስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማህበር ምክትል የቦርድ ሰብሳቢና የብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት ገልጸዋል።

በአሜሪካ የካሊፎርኒያ ሙዝየም የሚገኙ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅርስ የሆኑ መጽሃፍ ቅዱስና መስቀል በጨረታ ለመሸጥ ዝግጅት ላይ መሆኑን ማሳወቁን ገልጸው፤ቅርሶቹ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የወጡ በመሆናቸው መመለስ እንዳለባቸው የማሳመን ስራ እየተሰራ መሆኑንም አሉላ ፓንክረስት ገልጸዋል።

ቅርሶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ከዲያስፖራውና ሌሎች ድርጅቶች ጋር እየተሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የመገናኛ ብዙሃንን፣ ማህበራዊ ሚዲያንና ዲያስፖራውን በማስተባበር ቅርሶቹን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንና አስፈላጊ ከሆነ ገዝቶ ለማስመለስም ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

እንግሊዞች ከመቅደላ የዘረፏቸውን ዋንጫዎች፣ መጽሃፍ ቅዱስ፣ መስቀልና ሌሎች ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅርችን ለጨረታ አቅርበው እንደነበር አውስተዋል።

ጨረታው ቀርቶ በኢትዮጵያ ወዳጅ ድርጅቶች አማካኝነት ተገዝተው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባደረገው ድርድር በቅርቡ እንደሚመለሱም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በሆላንድ የተለያዩ የብራና መጽሃፎች በጨረታ መሸጣቸው ቀርቶ በአንድ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ ሆላንዳዊ ግለሰብ ተገዝተው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

እነዚህን ተሞክሮዎችን መነሻ በማድረግ የወጣው ጨረታው ትክክል አለመሆኑንና የተዘረፉ ቅርሶች መመለስ እንዳለባቸው ግፊት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ውጤት እንደሚመጣም ነው የኮሚቴው አባል የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም