በክልሉ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት ከነገ ጀምሮ በዘመቻ ይሰጣል

65

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 11/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ለመከላከል ከነገ ጀምሮ ክትባት በዘመቻ እንደሚሰጥ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የክትባት ዘመቻው በክልሉ በሚገኙ ከተሞችና በ196 ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች እንደሚካሄድ  የጤና ቢሮው ሃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ  ገልጸዋል።

ክትባቱ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች  ለሆኑ ህጻናት ከነገ ጀምሮ ለአራት  ቀናት እንደሚሰጥና በዚህም ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ይከተባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ  ተናግረዋል።

ቤት ለቤት የሚሰጠው ይሄው ክትባት ከዚህ ቀደም የተከተቡም  ሆነ ያልተከተቡ  ህጻናትን በሙሉ ባካተተ መልኩ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ቢሮው የክትባት አሰጣጥ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን  ለሀገር ሽማግሌዎች ፣የሃይማኖት መሪዎችና ለሌሎችም ሚመለከታቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ለማሳጨበጥ  ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

ክልሉ ክትባቱን  ለማስፈጸም  የጤና ባለሙያዎች ቡድን ማደራጀቱን የገለጹት ሃላፊው፤ ከፖሊዮ ዘመቻው ጎን ለጎን ኩፍኝና የሌሎች በሽታዎች ቅኝት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ህጻናትን የሚያጠቃው የፖሊዮ በሽታ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው ዳሰሳ 61  ህጻናት ላይ በመታየቱ ክትባቱ በዘመቻ እንዲሰጥ መወሰኑ  ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም