የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚሰሩ የጉጂ ኦሮሞ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለፁ

2683

ነገሌ ነሀሴ 12/2010 ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ድብቅ አላማቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ሀይሎችን በማጋለጥ ከመንግስት ጎን እንደሚቀሙ የገላና ወረዳ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች አስታወቁ፡፡

የጉጂ ኦሮሞ አባገዳ ተወካይ አቶ ጡራ ጂላ በሰጡት አስተያየት በስርአት አልበኝነት የተነሳ በተለይ በኢትዮ ሱማሌ ክልል፣ በጌዲኦና በጉጂ ኦሮሞ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት የደረሰውን ጉዳትና ጥፋት እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል፡፡

”ችግሩን ለማስቀረት የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች በምክንያት የሚያምን ወጣት እንዲፈጠርና ህግና ስርአት እንዲከበር መስራት ማስተማርና ማስረዳት አለብን” ብለዋል፡፡

ሌላው የጉጂ ኦሮሞ የአባገዳ አባል ቆንጮራ ጂና የእርስ በርስ ግጭት ለህዝብና ለሀገር ካለማሰብ የሚመጣ አሸናፊም ተሸናፊም የሌለበት ኋላቀር አስተሳሰብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የሰው ህይወት ማጥፋትና ንብረት ማቃጠል በኦሮሞ የገዳ ስርአት የሚወገዝ በመሆኑ ግጭቶችና አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ አስቀድሞ ማስተማር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ወጣቱን በማስተማር ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የጥፋት ሀይሎችን በማጋለጥ ለተጀመረው ለውጥ የድርሻቸውን ለማበርከት መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል፡፡

”ዘረኝነት፣ ቂምና በቀልን በመተው በሰላምና ልማት ተጠቃሚ ለመሆን ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን” ያሉት ደግሞ የሀገር ሽማግሌ አቶ ዩሐንስ አሬሪ ናቸው፡፡

”በሀገራችን በሁከትና ብጥብጥ ያለፉትን አመታት በሰላም፣ በስራና በልማት ማካካስ ይጠበቅብናል” ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት ወጣቱን ማስተማር፣ ማስተባበርና ለሰላምና ለስራ ማነሳሳት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የአባገዳዎች ያለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

መንግስትም ህግ ሲጣስ፣ የሰው ህይወት ሲጠፋና ንብረት ሲዘረፍ ከልክ ያለፈ ትእግስት ማድረግ እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡

በጉጂ ኦሮሞና በጌዲኦ መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከሁለቱም ወገን በርካታ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው መፈናቀላቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሰላም በመስፈኑና እርቀ ሰላም በመውረዱ አንዳንድ ነዋሪዎች ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው በመመለስ ላይ እንደሆኑ አቶ ዩሐንስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡