በደቡብ ወሎ ዞን ታሪፍ የጨመሩ አሽከርካሪዎች በወንጀል ተጠያቂ ናቸው

66

ጥቅምት 09/2014 /ኢዜአ/  በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ታሪፍ በመጨመር የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና የሚያሳድሩ አካላት በወንጀል እንደሚጠየቁ የደቡብ ወሎ ዞን አስታወቀ።
በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ችግር የሚፈጥሩ አካላት የህልውና ዘመቻውን በመፃረር ህግ እንደጣሱ ተቆጥሮ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ነው የተመለከተው።

በዞኑ የሚገኙ አሸከርካሪዎችና ባለንብረቶች ከታሪፍ በላይ ዋጋ በማስከፈል በህብረተሰቡ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን በደሴ የህዝብ ትራንስፖርት መናኸሪያ ምልከታ በማድረግ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ይህን ተከትሎ ከታሪፍ በላይ ዋጋ በማስከፈል በህብረተሰቡ እንቅስቃሴ ላይ ጫና የሚፈጥሩ አካላት በወንጀል እንደሚቀጡ ተገልጿል፡፡

ኢዜአ ባደረገው ምልከታ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ከታሪፍ በላይ ዋጋ በማስከፈል በህዝቡ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን መንገድ ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ከድር ይመር፤ ከታሪፍ በላይ በመጫን በህብረተሰቡ እንቅስቃሴ ላይ ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡

መምሪያው በአንድ ሳምንት ባደረገው የክትትልና ቁጥጥር ስራ ህግን በመተላለፍ ከታሪፍ በላይ ሲጭኑ የተገኙ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ 73 ሺህ ብር ለግለሰቦች እንዲመለስ አድርጓል፡፡

ህግን በተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ከ60 ሺ ብር በላይ ቅጣት የተጣለ ሲሆን፤ ከታሪፍ በላይ የጫኑ ተሸከርካሪዎችን ታርጋ በመፍታት እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ማህበረሰቡ ከህግና ከታሪፍ በላይ ባለመክፈል መብቱን መሞገትና ለመብቱ መከበር መታገል እንዳለበት ተናግረዋል።

በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ችግር የሚፈጥሩ አካላት የህልውና ዘመቻውን በመፃረር ህግ እንደጣሱ ተቆጥሮ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ድርጊታቸውም ህዝብን ለእንግልትና ስቃይ ከመዳረግ ባለፈ ከአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ኃይል ጋር ያላቸውን ተባባሪነት ስለሚያሳይ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ማወቅ አለባቸው ብለዋል፡፡

ህዝቡ ለሰራዊቱ ያለውን ደጀንነት በማስቀጠል የአሸባሪውን ህወሓት ምኞት በተባበረ ክንድ ማምከን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ማህበረሰቡም ምንም እንኳን በጦርነት ቀጣና ቢሆንም፤ ከመሸበር ወጥቶ በተረጋጋ መንፈስ መደበኛ ስራውን እንዲያከናውን አሳስበዋል፡፡

የትራንስፖርት ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች በማህበረሰቡ ላይ ጫና ከማሳደር በመቆጠብ አቅመ ደካሞችን ፣ ህፃናትን ፣ ነፍሰ ጡሮችንና ተጎጂዎችን ወደሚፈልጉበት ቦታ በማድረስ ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም