''በወሬ ሳንረበሽ የሽብር ቡድኑን ፊት ለፊት በመፋለም ህልውናችንን እናስቀጥላለን''--- የደሴ ከተማ ወጣቶች

62

ደሴ፤ ጥቅምት 11/2014 (ኢዜአ )፡ የህወሓት የሽብር ቡድን በሚያሰራጨው የሀሰት ወሬ ሳንረበሽ ወራሪውን ፊት ለፊት በመፋለም ህልውናችንን ለማረጋገጥ ግንባር ዘምተናል ሲሉ የደሴ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ።

የደሴ ከተማ ወጣቶች ከውይይት በኋላ ዛሬ ወደ ግንባር ዘምተዋል፡፡

ከደሴ ከተማ ወጣቶች መካከል ወጣት አሊ ይማም ለኢዜአ እንደገለጸው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአገርና በህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለው ጥፋትና ግፍ ታሪክን  ከማበላሸት ባለፈ የህብረተሰቡን የመኖር ህልውና አደጋ ላይ ጥሏል፡፡

የሽብር ቡድኑ በየጊዜው በሚነዛው ተለዋዋጭ የሀሰት ወሬ መረበሽ እንደማይገባ የጠቆመው ወጣት አሊ፤ ''በሀሰት ወሬው ተደናግጠን ከተማችንን መልቀቅ ሳይሆን ቡድኑን ተደራጅተን ለመፋለም ወደ ግንባር እየዘመትን ነው'' ብሏል፡

''እኛ ሸሽተን ማን መስዋት ሆኖ ነጻ ሊያወጣን ነው'' ያለው ወጣቱ "መሞት ካለብንም ተወልደን፤ ቦርቀንና ጭቃ አቡክተን ባደግንባት ከተማችን ላይ መስዋእት እንሆናለን እንጅ ታሪክ አናበላሽም" ሲል ገልጿል፡፡

ቡድኑ ተዋግቶ ሳይሆን በሀሰት ወሬ ህብረተሰቡን በማደናገር ከተማ የማሰለቀቅ ልምድ እንዳለው ያመለከተው ወጣት አሊ ''ደሴ ከተማ ላይ እኛ እያለን አይሳካለትም'' ሲል አስታውቋል።

ወጣት መሰረት ኃይሌ በበኩሏ ''ሁላችንም ወደ ግንባር በመዝመት ቡድኑን በመደምሰስ አካባቢያችንን ነጻ እናወጣለን'' ብላለች፡፡

በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ሁለንተናዊ ጥቃት ለመመከት እናቶች ልጆቻቸውን መርቀው መላክና ደጀን መሆን እንዳለባቸው አመልክታለች።

''የምንችለውን ጠጠር ወርውረን ኢትዮጵያን መታደግ እንጅ በወሬ ተፈተን የቡድኑን ምኞት ማሳካት የለብንም'' ያለው ደግሞ ወጣት ኤርሚያስ እሸቱ ነው፡፡

"ሀገር በጠላት ተወራ፣ ሰው ከመኖሪያ ቀየው እየተፈናቀለና እየሞተ እንዲሁም በጥረቱ ያፈራው ሀብትና ንብረት እየተዘረፈና እየወደመ እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት ወቅት አይደለም"" ሲል ተናግሯል።

''ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንጅ መደናገጥና መረበሽ የለበትም'' ያለው ወጣቱ ለሰራዊቱ ትጥቅና ስንቅ በማቀበል የኋላ ደጀንነቱን ማጠናከር እንዳለበት ጠቁሟል።

ወጣቶቹ ዛሬ ጠዋት ካደረጉት አጭር ውይይት በኋላም አሸባሪውን ቡድን በግንባር ለመፋለም መሰማራታቸውን አስታውቀዋል።

በሀሰተኛ ወሬ የተደናገጠውን የደሴ ከተማ ነዋሪ የከተማው ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል ዛሬ ሌሊት እየተዘዋወሩ ሲያረጋጉ ማደራቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም