ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና በመደጋገፍና በአንድነት ማለፍ ይገባል

119

ጥቅምት 11/2014 (ኢዜአ) "በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና በመደጋገፍና በአንድነት ማለፍ ይገባናል" ሲሉ ለአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ ዞን የህክምና መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ ለማድረግ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

በአፋር ክልል አሸባሪ ህወሃት ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ እናቶችና ህጻናትን እየገደለ መሆኑም ተገልጿል።
የጤና ሚኒስቴር በአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ ዞን በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት ስራ ማስጀመሪያ የህክምና መርጃ መሳሪያዎችን ዛሬ ድጋፍ አድርገዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ አፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተገኝተው ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ የህክምና መርጃ መሳሪያዎቹን አስረክበዋል።

ዶክተር ሊያ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና በመደጋገፍና በአንድነት ማለፍ ይገባል። ለክልሉ የተሰጠው ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።

የህክምና መርጃ መሳሪያዎቹ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ናቸው።

ሚኒስትሯ የዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታልንም ጎብኝተዋል።

አሸባሪው ህወሃት አፋርና አማራ ክልሎችን በመውራር የፈጸመው ኢ ሰብዓዊ ድርጊትና ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው። ንጹሃን ሰዎችን ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፣ ሴቶችን ደፍሯል፤ ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ፈጽሟል።

የተለያዩ መንግስታዊና ማህበራዊ ተቋማትን ዘርፏል። ለህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በመዝረፍና በማውደም ቁሳዊና ማህበራዊ ጉዳት አድርሷል። ከነዚህ መካከል የጤና ተቋማት ይገኙበታል።

ጤና ሚኒስቴር የህክምና መረጃ ቁሳቁስ ድጋፋ ያደረገው በክልሉ በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው አምስት የጤና ተቋማት ስራ ለማስጀመር መሆኑ ነው የተገለጸው።

የሚኒስቴሩ ድጋፍ የህክምና ተቋማቱ ወደ ስራ እንዲገቡና ድንገተኛና መደበኛ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ እገዛ እንደሚያደርግ ዶክተር ሊያ ጠቁመዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተደድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሓት በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ ንጹሐንን ገድሏል፤ የዜጎች ሀብት ላይ ዘረፋ ፈጽሟል።

ይህ አሸባሪ ቡድን ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ እናቶችና ህጻናትን እየገደለ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም ከሰሞኑ በጭፍራ ወረዳ ላይ በከባድ መሳሪያ ድብደባ በመፈፀም እናቶች፣ ህጻናትና አረጋዊያን ላይ ግድያ መፈጸሙን አስታውሰዋል።

የዚህ ጨካኝና አረመኔ ቡድን ድርጊት ለታሪክ የሚቀመጥ መሆኑን ገልጸው፤ የጤና ሚኒስቴር በወሳኝ ወቅት ድጋፍ በማድረጉ ምስጋና ችረዋል።

ይህ አሸባሪ ቡድን ድርጊት "በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ይመከታል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም