በሰሜን ወሎ ዞን በንግድ ተቋማት ሚዛኖች ላይ በተካሄደ ምርመራ በ900 ያህሉ ጉድለት ተገኘ

49
ወልድያ ነሃሴ 12/2010 በሰሜን ወሎ ዞን በተለያዩ የንግድ ተቋማት ሚዛኖች ላይ በተካሄደ ዓመታዊ ምርመራ በ900 ያህሉ ጉድለት መገኘቱን የሰሜን ወሎ ዞን የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የውጭ ድህረ ፈቃድ ቡድን መሪ አቶ ተከታይ ደሴ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አገልግሎት በሚሰጡ 27 ሺህ 886 ልዩ ልዩ ሚዛኖች ላይ ፍተሻ ተካሄዷል። ከተፈተሹትና ከተመረመሩት ሚዛኖች ውስጥም 897 ሚዛኖች በእያንዳንዳቸው ከአንድ ኪሎ ግራም ላይ እስከ 250 ግራም ጉድለት ተገኝቶባቸዋል፡፡ ''የጉድለቱ ምክንያትም የግራሙን ድንጋይ ውስጡን ቦርቡሮ በቀላል ነገር በመሙላትና የሚዛኑን የውስጥ ክፍል በማዛባት መሆኑ ተደርሶበታል'' ብለዋል። ጉድለት የተገኘባቸው ሚዛኖችም በሥጋ ቤቶች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ሱቆች እንዲሁም በእህል ሚዛኖች ላይ መሆኑን አመልክተዋል። በተጨማሪም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው 6ሺህ 317 ሊትር የታሸጉ ጭማቂ መጠጦች፣ የመዋቢያ ቅባቶችና አንድ ሺህ ኪሎ ግራም የሚጠጋ ጠጣር እሽግ ምግቦች ተገኝተው እንዲወገዱ ተደርጓል። ጊዜ ያለፈባቸው የነዳጅ መቅጃ ማሽኖችን ጨምሮ ጉደለት የተገኘባቸው ሚዛኖች እንዲወገዱ የተደረገ ሲሆን ለአንቀሳቃሾች ማስጠንቀቂያ የከፋ ችግር ያለባቸው ድርጅቶችን ደግሞ የማሸግ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል። የምርት ተጠቃሚ ከሆነት መካከል አቶ አብርሃም መኮንን እንዳሉት በግብይት ወቅት ሚዛንንም ሆነ የምርቶች ጊዜ ያለፈባቸው ይሁን አይሁን ትኩረት እንደማይሰጡ ተናግረዋል። ካሁን በኋላ ግን ሸቀጦችን ለመግዛት ሲያስቡ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ሌላው የወልድያ ከተማ ነዋሪ አቶ ደሳለ ካሳ እንዳሉት ችግሩ መኖሩን ጥርጣሬ ቢኖራቸውም በተለይም በሚዛንና በመመዘኛ ድንጋዩ ላይ ያለውን ችግር እንዴት መጠየቅ እንደሚቻል ግንዛቤው የላቸውም።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም