በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሚሰጣቸው የማጠናከሪያ ትምህርት ለውጤታቸው መሻሻል አስተዋጽኦ ማድረጉን የሚኤሶ ወረዳ ተማሪዎች ገለፁ

62
ጭሮ /ነቀምት ነሀሴ 12/2010 በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሚሰጣቸው የማጠናከሪያ ትምህርት ለውጤታቸው መሻሻል ከፍተኛ አስተዋኦ እያደረገ መሆኑን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የሚኤሶ ወረዳ ተማሪዎች አስታወቁ። በወረዳው የ11ኛ ክፍል ተማሪ ኢብሳ ኢብራሂም እንደሚለው በክረምት ወራት በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የሚሰጠውን የማጠናከሪያ ትምህርት መከታተል ከጀመረ አራት ዓመት አስቆጥሯል። በነዚህ ጊዜያት  የትምህርት ውጤቱን በማሻሻል ከክፍሉ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ነው የሚናገረው። በመጪው ዓመት ለብሔራዊ ፈተና  በግሉ ከሚያደርገው ዝግጅት ጎን ለጎን  በዘንድሮም የማጠናከሪያ ትምህርት ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጿል፡፡ ተማሪ ሪስቆ አብደላ በበኩሏ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሚሰጠው ነፃ የማጠናከርያ ትምህርት ለመጪው የትምህርት ዘመን አቅም ለመገንባት እንደሚረዳት ገልፃለች፡፡ እንዲሁም ካሁን በፊት በግል ትምህርት ቤት ለማጠናክሪያ ትምህርት የምትከፍለውን ወጪ ማዳን እንዳስቻላት ተናግራለች፡፡ ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና ተማሪ ሳምራዊት ሶሎሞን ያላትን እውቀት ለታናናሾቿ በማካፈሏ መደሰቷን ገልጿለች፡፡ የሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ ዘላለም አበበ በበኩሉ በግንዛቤ ማነስ ባለፉት ሶስት ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባለመሳተፉ ተቆጭቷል። ዘንድሮ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ በመቀጠል ሳይማር ያስተማረውን ማህበረሰብ ለመካስ እንደሚቀሳቀስ አረጋግጧል። የሚኤሶ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፋሚ ጀማል በበጎ ፈቃደኛ የዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች አማካኝነት በ37 ትምህርት ቤቶች የማጠናከሪያ ትምህረት እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በምስራቅ ወለጋ ዞን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች ከ795 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የልማት ስራ ማከናወናቸውን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ገልጿል። በጽህፈት ቤቱ የወጣቶች ንቅናቄ እና ስርፀት ስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ ታደሰ እንዳሉት በወጣቶቹ የልማት ስራው የተከናወነው ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነው። በ39 የስራ ዘርፎች በመሰማራት ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል የውስጥ ለውስጥ መንገድ ጥገና፣ የከተማ ጽዳትና ውበት፣ የአቅመ ደካማ ነዋሪዎች ቤት ጥገና፣ ደም ልገሳ፣ ችግኝ ተከላና የማጠናከርያ ትምህርት መስጠት ይገኝበታል። በዚሁ እንቅሳቀሴ ላይ ከ66 ሺህ የሚጠጉ የዞኑ ወጣቶች መሳተፋቸውን ገልጸው አገልግሎታቸውም እስከ ዻጉሜ ይቀጥላል። የጉቶ ጊዳ ወረዳ የቅጠሳ ቀበሌ ወጣት አያና ታሪኩ በግንዛቤ ማነስ ደም ለመለገስ ፈቃደኛ እንዳልነበረ ገልፆ ለመጀመሪያ ጊዜ ደም በመለገስ በአገልግሎቱ መሳተፉን ተናግሯል። የጅማ አርጆ ወረዳ የ02 ቀበሌ ነዋሪ እና የመቱ መምህራን ኮሌጅ እጩ መምህርት ወጣት ማርታ አበራ በበኩሏ በልዩ ልዩ አገልግሎት ከመሳተፍ ባለፈ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ህሙማንን በመጎብኘት የደም እጥረት ላጋጠማቸው ደም መለገሷን ገልፃለች።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም