ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ 210 ኪሎ ግራም አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ስር ዋለ

92

ነገሌ፤ ጥቅምት 10/2014(ኢዜአ) በጉጂ ዞን ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ 210 ኪሎ ግራም አደንዛዥ እጽ ከአንድ ተጠርጣሪ ጋር እጅ ከፍንጅ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

አደንዛዥ እጹ መነሻውን በዞኑ አዶላ ወዩ ከተማ አድርጎ  ወደ አጋ ዋዩ ወረዳ  ሲጓጓዝ ዛሬ ጥዋት መቆጣጠር እንደተቻለ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የጸጥታና ሰላም ማስከበር ምክትል ዳይሬክተር ዋና ሳጂን ጉተማ ሳፌ ታርጋ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በሞተር  ብስክሌት ተጭኖ ሲጓጓዝ  የነበረው አደንዛዥ እጽ 210 ኪሎ ግራም የሚመዝን ነው ብለዋል፡፡

እጅ ከፍንጅ የተደረሰበት አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ገልጸው፤ ለጊዜው ሸሽተው ያመለጡ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን አድኖ ለመያዝ ክትትሉ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረው አደንዛዥ እጽ መቆጣጠር የተቻለው የአዶላ ከተማና የአጋ ወዩ ወረዳ ህዝብ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎች ስልታቸውን በመቀያየር ገጠር ለገጠር በማጓጓዝ የጥፋት ዓላማቸውን ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ለሽብር የወንጀል ተግባር የሚውል የአደንዛዥ እጽ ዝውውር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመሆኑ የዞኑ ህዝብ ጥቆማ በመስጠት የጀመረውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና ሳጂን ጉተማ ጠይቀዋል፡፡

ጥቅምት 5/2/2014 ዓ.ም በአዶላ ሬዴ ወረዳ አዳማ ዲባ በተባለ ገጠር ቀበሌ ውስጥ ታርጋ በሌለው ሞተር ተጭኖ ሲጓጓዝ የነበረ 119 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዝ እጽ መያዙን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም