ከወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሚደርስ የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል

111

አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2014 (ኢዜአ) ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ከወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሚቃጣውን የሳይበር ጥቃት መከላከል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ገለጸ።

በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚሰነዘረውን የሳይበር ጥቃት በብቃት ለመመከት ተቋማት ግልጽ የሆነ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ፖሊሲ ሊኖራቸው ይገባልም ተብሏል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ሁለተኛውን የሳይበር ደህንነት ወር "የጋራ ሀላፊነት ለሳይበር ደህንነት እንወቅ እንጠንቀቅ" በሚል መሪ ሃሳብ እያከበረ ነው።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንተነህ ተስፋዬ ለኢዜአ እንዳሉት የሳይበር ጥቃት ከአምስቱ የዓለም የደህንነት ስጋቶች አንዱ ነው።

የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የስጋት ትንተናን ዓመታዊ ሪፖርት ዋቢ በማድረግ እንደጠቀሱት እ.አ.አ በ2020 ዓለም በሳይበር ጥቃት አማካኝነት ሁለት ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሟታል።

የፎረሙ የስጋት ትንተና ትንበያ እንደሚያመለክተው በ2025 በሳይበር ጥቃት የሚደርሰው ኪሳራ ወደ ስድስት ትሪሊዮን ዶላር ከፍ ይላል ብለዋል።

በኢትዮጵያም የሳይበር ደህንነት አሳሳቢነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው በ2012 ዓ.ም ከአንድ ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ተከስቶ ምላሽ እንደተሰጠ ጠቁመዋል።

የሳይበር ጥቃት የሰዎችን አዕምሮና ዓለም አቀፍ እይታዎችን በፍጥነት የሚለውጥና የሚያዛባ ከመሆኑም በላይ በተቋምም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ጉዳት ያደርሳል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃትን በተመለከተ የህብረተሰቡ ግንዛቤ ውስን መሆኑን የገለጹት ዶክተር አንተነህ  ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ከአገራዊ የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ኖሮት መከላከል እንዲችል "ኢትዮ ሳይበር" የተሰኘ ራሱን የቻለ ማዕከል ተቋቁሟል፤ ባለሙያዎችም በየተቋማቱ እየተዘዋወሩ የሳይበር መረጃዎችን ይሰጣሉ ብለዋል።

በተጨማሪም ተቋሙ የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሚያስችሉ አንቲ ቫይረስና ሌሎች ሶፍትዌሮች እንደሚያበለፅግ ገልጸዋል።

ከአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በመገናኛ ብዙሃን ማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መድረሱን የገለጹት ደግሞ የኤጀንሲው የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያ አቶ አሸናፊ ሀይሉ ናቸው።

በመሆኑም ማህበራዊ ድረ ገጾች ያሏቸው ተቋማት የሳይበር ጥቃትን መከላከል እንዲችሉ የማህበራዊ ድረ ገፆችን አጠቃቀም የሚመራ ፖሊሲ ሊያወጡ ይገባል ይላሉ።

እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ቀመር በ2020 በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ ብቻ ባነጣጠረ የሳይበር ጥቃት 94 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም