የቱሪስት መስህቦች ትኩረት በማጣታቸው ጥቅም ላይ አልዋሉም

281

መቱ፣ ጥቅምት 10/2014 (ኢዜአ) ለአካባቢውም ሆነ ለሀገር ዕድገት አስተዋፆ ያላቸው ትላልቅ የቱሪዝም መስህቦች ትኩረት በማጣታቸው ጥቅም ላይ ሊውሉ አልቻሉም ሲሉ የኢሉ አባቦር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ ።

በዞኑ "ቱሪዝም ለሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ ሀሉ ወረዳ ኡካ ከተማ የዓለም ቱሪዝም ቀን ተከብሯል ።

ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ተወጣጥተው በበአሉ ላይ የታደሙ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የተለያዩ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች ቢኖሩም ለአካባቢው የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ሥራ ባለመሰራቱ ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊውሉ አልቻሉም ።

ከኖኖ-ሰሌ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ብርሃኔ ሒርከታ እንዳሉት ቱሪዝም ለአንድ አካባቢም ሆነ ሀገር ትልቅ ሀብትና የዕድገት ምንጭ ቢሆንም በዞኑ ለመስህቦች ትኩረት ባለመሰጠቱ ጥቅም ላይ ሳይውሉ ቀርተዋል ።

በዞኑ የሚገኙና  ለሀገር ዕድገት ትልቅ ሀብት ሊያመጡ የሚችሉ የቱሪስት መስህቦች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አመልክተዋል ።

የያዮ ወረዳ ነዋሪ አቶ ተመስገን ዓለማየሁ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙና ሀገርን መለወጥ የሚችሉ የቱሪዝም ሀብቶችን የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራ በትኩረት ስላልተሠራባቸው ጥቅም ላይ ያለመዋላቸውን ተናግረዋል።

"ሌላው ቀርቶ በዩኔስኮ የተመዘገበው የያዮ ተፈጥሯዊ ደን ትልቅ የገቢ ምንጭ መሆን ቢችልም ከስም ያለፈ ለምንም ያልዋለ ሀብት ሆኖ ቀርቷል" ሲሉ ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ዞኑ ጢስ አልባ ኢንዱስትሪ በመባል በሚታወቀው የደን ሀብትና ሌሎች ተፈጥሯዊ መስህቦች ባለቤት በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

"ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም ለማስገኘት የቱሪዝም ቀንን ማክበር ብቻውን በቂ አይደለም፤ ውጤታማም አያደርግም" ያሉት ደግሞ የቡሬ ወረዳ ነዋሪ አባ ገዳ ታደሰ ዳባ ናቸው።

በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶች ለሀገር እንዲጠቅሙ ለማድረግ  ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጀምሮ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል ።

በኢሉአባቦር ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም ማስፋፊያና ፕሮሞሽን የሥራ ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ተመስገን ኮርጄ በዞኑ የሚገኙ አብዛኛው የቱሪዝም ሀብቶችን የመለየት ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል ።

ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራ ሊሠራባቸው የሚገቡትን በቅደም ተከተል የማስቀመጥ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሶርና የኢሊኬ ፏፏቴዎችን የማልማትና ለአካባቢውም ሆነ ለሀገር ጥቅም  የማዋል ተግባራት ከክልልና ፌደራል መንግስታት ባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት ለመሥራት መታቀዱንና የማስተዋወቅ ስራ መጀመሩን አመልክተዋል።

በኢሉባቦር ዞን የተለያዩ ትላልቅ ፏፏቴዎች፣ ዋሻዎች፣ ደኖችና ታሪካዊ ቦታዎች መኖራቸውን የዞኑ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም