119 ኪሎ ግራም አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ስር ዋለ

111

ነገሌ ፤ ጥቅምት 9/2014(ኢዜአ) በጉጂ ዞን የአዶላ ሬዴ ወረዳ በሞተር ብስክሌት ሲጓጓዝ የነበረ 119 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የወረዳው  ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አብዱልከሪም ሁሴን እንደገለጹት፤  አደንዛዥ እጹ በቁጥጥር ስር የዋለው ጥቅምት  5/2014ዓ.ም.  ጭለማን ተገን በማድረግ ወደ ነገሌ ከተማ ሲጓጓዝ በህብረተሰቡ ጥቆማ ተደርሶበት ነው፡፡

የሰሌዳ ቁጥር  በሌለው ሞተር  ብስክሌት  ተጭኖ በገጠር ውስጥ ለውስጥ መንገድ ሲጓጓዝ  የነበረው አደንዛዥ እጹ  አዳማ ዲባ በተባለ ገጠር ቀበሌ  መቆጣጠር እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

የሞተር ብስክሌቱ አሽከርካሪ  ለጊዜው ሞተሩንና  አደንዛዥ እጹን ጥሎ  ከአካባቢው ሸሽቶ ቢያመልጥም ለመያዝ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን አስረድተዋል።

የወረዳው ህዝብ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ላደረገው ትብብር ምስጋና ያቀረቡት ኢንስፔክተር አብዱልከሪም፤ ህገ ወጦችን ለመከላከል የህብረተሰቡ ትብብር እንዲቀጥልም አመልክተዋል።

ህገ ወጦች  በዋና ዋና መንገድና በከተማ የሚያደርጉት የእንቅስቃሴ ስልት ሲነቃባቸው አሁን ደግሞ የገጠር መንገድን እንደ አማራጭ እየተጠቀሙ ነው ብለዋል አዛዡ፡፡

የወረዳው ፖሊስ  ሀሰተኛ የብር ኖት፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ እና  አደንዛዥ  እጽ ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሚገኝ  ገልጸዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም