በጉጂ ዞን ለሽብር ድርጊት ሊውል የነበረ 4 ሺህ 818 ተተኳሽ ጥይት ከተጠርጣሪው ጋር ተያዘ

84

ነገሌ፣ ጥቅምት 7/2014 (ኢዜአ) ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ 4 ሺህ 818 ተተኳሽ ጥይት ከተጠርጣሪው ጋር መያዙን በኦሮሚያ ክልል የጉጂ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የአካባቢ ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ምክትል ዳይሬክተር ዋና ሳጂን ጉተማ ሳፋይ እንደገለጹት ተተኳሽ ጥይቱ ሊያዝ የቻለው ፖሊስ ከዞኑ ህዝብና ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ጋር ባደረገው ክትትል አማካኝነት ነው።

ተተኳሽ ጥይቱ ነገሌ ከተማ ሊገባ 15 ኪሎ ሜትር ሲቀረው በዞኑ ጎሮዶላ ወረዳ ቢታታ ቀበሌ ላይ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-54895 አዲስ አበባ በሆነ የግል ተሽከርካሪ ሲጓጓዝ ትላንት ምሽት ከተጠርጣሪው ግለሰብ ጋር የተያዘ መሆኑን ተናግረዋል።

መነሻውን ከአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ያደረገውን ተተኳሽ ጥይት ለሽብርተኛው ሸኔ እንዲያደርስ በማያውቀው ሰው በስልክ ተነግሮት በባጃጅ እንደተላከለትና ነገሌ ለሚጠብቀው ሌላ ሰው ለማስረከብ እየተጓዘ እንደነበረ ተጠርጣሪው ለፖሊስ በሰጠው ቃል መግለጹን አብራርተዋል፡፡

ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ኪሱን ሲፈትሽ 16 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ይዞ መገኘቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ተጨማሪ ህገ-ወጥ ተግባር እንዳይፈጸምም ፖሊስ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ላይ ሲሆን እጅ ከፍንጅ የተያዘው ተጠርጣሪ ጉዳይም ተጨማሪ የማጣራት ስራ እየተከናወነበት እንደሚገኝ አስረድተዋል።

"ሽብርተኛው ሸኔ ከጥፋት ተባባሪው ህወሀት ተልእኮ በመቀበል ሀገር ለማፍረስ በጉጂ ዞን በንጹሀን ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ይገኛል" ብለዋል፡፡

ይሔንን በንጹሀን ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ለመከላከልም የዞኑ ህዝብ ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ላለው ድጋፍና ትብብር ምስጋና አቅርበው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም