የግል ኮሌጆችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር የስራ ፈጠራን ማሳደግ ያስፈልጋል

66

አሶሳ ፤ ጥቅምት 06 / 2014 (ኢዜአ) የግል ኮሌጆችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር የተመራቂ ወጣቶችን የስራ ፈጠራ ክህሎት ማዳበርና ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተመለከተ፡፡
"ኤም.ኤ. " ኮሌጅ ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ  ጋር በመተባበር  ያዘጋጁት የጥናት እና ምርምር መድረክ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሃየሎም አብረሃ በመድረኩ “የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ እና ከትምህርት ወደ ስራ ሽግግር ፤ ለዘላቂ ሃገራዊ ልማት” በሚል የግል ኮሌጆች ላይ ያተኮረ ሃገር አቀፍ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

ጥናቱ እንደሚያመላክተው፤ በሃገሪቱ የሚገኙ የግል ኮሌጆች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን የያዙ ቢሆንም ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያላቸው ትስስር እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡

የግል ኮሌጆች ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ለተማሪዎች በሚሰጡት የተግባር ልምምድ የተገደበ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል  ብለዋል አቅራቢው፡፡

በተቋማቱ መካከል የተቀናጀ አሰራር አለመኖሩ ዋነኛ ችግር እንደሆነ ጥናቱ እንደሚሳይ  አመልክተዋል፡፡

የግንዛቤ ማነስ፣ የተቋማት አደረጃጀትና አንዳቸው በሌላቸው ላይ ያላቸው እምነት ማነስ፣ የጋራ ሃገራዊ ራዕይ አለመኖር ከተጠቀሱት ችግርች ይገኙበታል፡፡

የግል ኮሌጆች እና ኢንዱስትሪዎች የጋራ ሃገራዊ ራዕይ በማስቀመጥ በጀትን አቀናጅቶ ከመጠቀም ጀምሮ በትብብር መስራት እንዳለባቸው በጥናቱ የተመላከተ መፍትሄ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ይህም በግል ኮሌጆች የሚመረቁ ወጣቶች ከጠባቂነት ይልቅ ስራ በመፍጠር አምራች ዜጋን ማፍራት እንደሚያስችል ጥናቱ ማመላከቱን ረዳት ፕሮፌሰር ሃየሎም አስረድተዋል፡፡

በግልም ሆነ በመንግስት ኮሌጆች የሚዘጋጁ የስራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠናዎች በትምህርት ዘመን ማብቂያ የሚሰጡ ቢሆንም  በቂ እንዳይደለ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ተነስቷል፡፡

ይህም ተመራቂ ወጣቶች ከስራ ጠባቂነት እንዲላቀቁ በቂ አቅም እንዳኖራቸው ማድረጉን ጠቁመው፤  የስራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሊጀመር እንደሚገባ ነው የተመለከተው፡፡

እንዲሁም በራሳቸው የሚተማመኑ ወጣቶችን ለማፍራት እየተበራከተ የመጣውን አደንዛዥ እጾች መከላከል እና የመዝናኛ ማዕከላትን ማብዛት እንደሚስፈልግ ተገልጿል፡፡

የኤም.ኤ. ኮሌጅ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ክንዴ ፤ በኮሌጁ ትምህርት የሚከታተሉ ተማሪዎች በስልጠና ወቅት ገንዘብ እንዲቆጥቡ በማድረግ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ስራ መፍጠር የሚያስችል ካፒታል እንዲኖራቸው ጥረት መደረጉን  አስረድተዋል፡፡

በዚህም በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ኮሌጁ ለማህበረሰቡ ለውጥ የሚያደርገው ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የቴክኒክ ኮሌጆች የስራ እድል ፈጠራ ለማጠናከር ያላቸው ግንኙነት እና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመድረኩ ከ50 የሚበልጡ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም