በቀን አንድ ሚሊዮን ዳቦ የሚያመርተው የዳቦ ፋብሪካ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

330

ጥቅምት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ የተገነባው በቀን አንድ ሚሊዮን ዳቦ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
ጽህፈት ቤቱ በመዲናዋ ለሚ ኩራ ክፍለከተማ በ217 ሚሊዮን ብር ወጭ ያስገነባው የዳቦ ፋብሪካ ዛሬ ለምረቃ በቅቷል።

የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት ያስገነባውን የዳቦ ፋብሪካ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስረክበዋል።

ከንቲባዋ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው ዳቦ ፋብሪካ ለከተማዋ አንድ እሴት እንደሚጨምር ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።

የዳቦ ፋብሪካው በአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም በሚከሰት የኑሮ ውድነት ዝቅተኛና ምንም ገቢ ለሌለው የማህበረሰብ ክፍል ላይ የሚደርሰውን ጫና በማቃለል በኩል ያለውን አስተዋጽኦም ገልጸዋል።

ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው በገጠር አካባቢዎች ትምህርት ቤት ማግኘት ለማይችሉ ህጻናት በአጭር ጊዜ በርካታ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ በማውሳት በዳቦ አቅርቦትም እያደረጉ ያለው አስተዋጽኦ በምሳሌነት የሚጠቅስ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን የመለወጥ ሂደት በአንድ አካል ብቻ ተሰርቶ የሚየመጣ ባለመሆኑ የዝቅተኛ የማህበረሰብ ክፍሎችን ጫና በማቃለልና በሌሎች የልማት ስራዎች መረባረብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ዳቦ ፋብሪካው ከሚፈጥረው የስራ እድል በተጨማሪ ምርቱን በመሸጥ ኑሯቸውን እንዲደጉሙና ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ የመሸጫ ቦታ በማዘጋጀት ለእናቶች ቅድሚያ ይሰጣል ብለዋል።

ከፋብሪካው ወደ መሸጫ ቦታ የዳቦ ምርቱን ለማጓጓዝ ባለሃብቶች የተሽከርካሪ ድጋፍ እንዲያደርጉም ከንቲባዋ ጠይቀዋል።

እንደ ከንቲባዋ ገለጻ በሸገር ዳቦ ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙ ልምድ በመውሰድ ይተገበራል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በበኩላቸው ፋብሪካው ለድሃው ህብረተሰብና ለከተማዋ ነዋሪ በዳቦ አቅርቦት በኩል የሚኖረውን አስተዋጽኦ አስረድተዋል።

ለ450 ሰዎች የስራ እድል የሚፈጥረው ፋብሪካው በሶስት ፈረቃ 24 ሠዓት የሚሰራ ሲሆን በቀን አንድ ሚሊዮን ዳቦ የማምረት አቅም አለው።

የዳቦ ፋብሪካው መከፈቱ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በተለያየ ሙያ እያገለገሉ የሚገኙ አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል።

የዳቦ ፋብሪካው ጎን ለጎን በቀን 72 ቶን ዱቄት የሚያመርት ሲሆን ቀደም ሲል የተገነቡ የዳቦ ፋብሪካዎች የገጠማቸው የስንዴ አቅርቦት ችግር እንዳይገጥመው እየተሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም