1 ሺህ 496ኛው የመውሊድ በዓል ሰኞ ይከበራል

117

ጥቅምት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) 1 ሺህ 496ኛው የነብዩ መሀመድ ልደት (መውሊድ) ከነገ በስትያ ሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚከበር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
በዓሉን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

"ነቢዩ መሐመድ የተወለዱት መልካም ነገሮችን ሊያስተምሩና መጥፎ ነገሮችን ደግሞ ሊቃወሙ በመሆኑ መልካም ስራቸውን በማየት በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ መውሊድ ይከበራል" ብለዋል።

በዓሉ ሲከበር የነቢዩ መሐመድን በረከቶች በማስተዋልና መንገዳቸውን በማሰብ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር አቅም የሌላቸውን በመጎብኘትና ካለው በማካፈል እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲው በአገሪቷ ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ገንዘብ በማሰባሰብ በሠላም ሚኒስቴር በኩል በተዘጋጀ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።

መንግስት በተለያየ ችግር ላይ ያሉ ዜጎችን መደገፍና ድጋፉም ለተጎዱ መድረሱን ሊያረጋግጥ እንደሚገባም  ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ አመልክተዋል።

የመውሊድ በዓል የሠላም እንዲሆን መልካም ምኞታቸውንም አስተላልፈዋል።

"አገራችንን አማን አላህ ያድርግልን፣ የአውሬ ጸባይ ከሰው ጸባይ ላይ አላህ ያንሳልን፣ የሚያፈቃቅር የሚያቀራርብ የሚያመካክር ነገር አላህ ይስጠን" ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም