በአማራ ክልል በበጋ ወራት ከ239ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው

67

ባህርዳር ጥቅምት 6/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ239ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የበጋ መስኖ ልማቱ የሚከናወነው በህወሃት ወራሪ ኃይል በመኽር የጠፋውን ሰብል ለማካካስ  ጭምር መሆኑን ተመልክቷል።

ከአንድ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በማሳተፍ   ከሚለማው መሬትም 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ግብ መቀመጡን በቢሮው የመስኖ ውሃ አጠቃቀም፣ አትልትና ፍራፍሬ ልማት ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድምነው ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከ108 ሺህ ሄክታር የሚበልጠው በቆላ ስንዴ  በመስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ እንደሚገኝበትና ገጠም አስተራረስም በስፋት ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት።

ልማቱም  በክልሉ በሚገኙ አነስተኛ እስከ ከፍተኛ ግድቦች በመታገዝ እንደሚከናወንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

 በአሁኑ ወቅትም ከፀጥታ ችግር ነፃ በሆኑ አካባቢዎች የሚለማ መሬት የመለየት፤  የጓሮ አትክልት ችግኝ ዝግጅት፣ የመስኖ አውታሮች ቦይ ጠረጋና የእርሻ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግም 513 ሺህ 200 ኩንታል ማዳበሪያና 129 ሺህ 276 ኩንታል ዘር ጥቅም ላይ እንደሚውልም አቶ ይበልጣል አስረድተዋል።

እንዲሁም 33 ሺህ 730 የውሃ መሳቢያ ሞተሮች፣  ከ181 ሺህ በላይ የእጅ ውሃ ጉድጓዶችና የማህበረሰብ ኩሬዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ ብለዋል።

በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ የይጎማ ሁለቱ ቀበሌ   አርሶ አደር አደባባይ ሰማ  በሰጡት አስተያየት፤ ሁለት ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት  የእርሻ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የመሬት ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ከቀጣዩ ወር አጋማሽ በኋላ ጀምሮ  በውሃ መሳቢያ ሞተር ታግዘው ጤፍና ጓሮ አትክልት እንደሚያለሙ ነው የገለጹት።

የዚሁ ቀበሌ  አርሶ አደር ፈንታሁን ትዕዛዙ በበኩላቸው፤ ከአንድ ሄክታር ተኩል በላይ መሬት  በባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ በመታገዝ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ውሃን በቁጠባ ተጠቅመው  የብርዕና የአትክልት አልመተው  ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት  አደርጋለሁ ብለዋል።

በአማራ ክልል  ባለፈው ዓመት የበጋ ወራት በመስኖ ከለማው መሬት ከ37 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም