ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በሚፈጠሩ ችግሮች ሳይሸነፍ የነገ ብሩህ ተስፋዋን ዕውን የሚያደርግ አመራር ነው

102

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05/ 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በየጊዜው በሚፈጠሩ ችግሮች ሳይሸነፍ የነገ ብሩህ ተስፋዋን ዕውን የሚያደረግ አመራር ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ያሉት በአፍሪካ ልህቀት ማዕከል ሲሰጥ የነበረውን የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ማጠናቀቂያ መድረክ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ ችግሮች ቢበዙም የነገዋ ኢትዮጵያ ግን በብሩህ ተስፋ የተሞላች ናት ብለዋል።

በመሆኑም አመራሩ በየጊዜው በሚያጋጥሙ ችግሮች ሳይሸነፍ የተሻለ ነገን ዕውን ለማድረግ ሊተጋ ይገባል ነው ያሉት።

ችግርን የሚተነትን ብዙ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ አመራሩ ከችግሮች ባሻገር ያለውን ብሩህ ተስፋ በተግባር ማሳየት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡

የውሸት ሪፖርት ሕዝብ ያማረረ ሌላኛው ጉዳይ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አመራሩ በወረቀት በሚቀርብ ሪፖርት ላይ ሳይወሰን ስራዎችን እስከታች በመውረድ መከታተል አለበት ነው ያሉት፡፡

በውዳሴ ብዛት ሳትዘናጉና በሚገጥማችሁ ጉንተላ ሳትሸማቀቁ ሕዝብን በቅንንነት ማገልገል አለባችሁ ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት፡፡

አጀንዳ ለመፍጠር አመራሩ ላይ ትኩረት አድርገው የተጋነነ ማወደስና ተገቢ ባልሆነ መንገድ የማሸማቀቅ ስራ የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን በማንሳት፡፡

ተቋም አመራሩን ይመስላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አመራሩ ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል ከሰራ ሠራተኞቹም የእርሱን ዓርአያ ይከተላሉ ብለዋል፡፡

ኃላፊነት የተሰጣቸው አመራሮች የሚያገለግሉት ሕዝብ በበርካታ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኝ በመገንዘብ ስራዎቻቸውን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ እንዲከውኑም አሳስበዋል።

ላለፉት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው የአዳዲስ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና በሁሉም ክልሎች ተሿሚ አመራሮች ዘንድ እንደሚቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም