የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በናይሮቢ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከፈተ

109

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በናይሮቢ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን መክፈቱ ተገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ በኬኒያ የሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትን የሚያካትት ነው ተብሏል።

ትናንት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሲከፈት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ሊቀ-ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ በኬኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለምና የኬኒያ የሃይማኖት የተቋማት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አባ ጆሴፍ ሙቲ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያን ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የጽህፈት ቤቱ መከፈት በኬኒያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሃይማኖታዊና አገራዊ ጉዳዮች እንዲግባቡ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

ጽህፈት ቤቱ ከኬኒያ የሃይማኖት ተቋም ምክር ቤት ጋር በመቀናጀት የሁለቱን አገራት ሕዝቦች ትስስር ለማጠናከር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም፤ የጽህፈት ቤቱ መከፈት የሁለቱን አገራት ህዝቦች አንድነት ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።

የኬኒያ የሃይማኖት የተቋማት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አባ ጆሴፍ ሙቲ፤ ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የኬኒያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የጽህፈት ቤቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንደተሰየሙ ኢዜአ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቀደም ሲል በዋሺንግተን ዲሲና ሮም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የከፈተ ሲሆን የናይሮቢው ሶስተኛው ቅርንጫፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም