"ትናንት ዛሬና ነገን በማስተሳሰር የምንፈልጋትን አፍሪካ መገንባት አለብን"

74

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ትናንት ዛሬና ነገን በማስተሳሰር የምንፈልጋትን አፍሪካ መገንባት አለብን" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን፤ በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት  የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ለሚካፈሉ የተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በወዳጅነት ፓርክ የእራት ግብዣ አድርገውላቸዋል፡፡

በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክትም "ትናንት ዛሬና ነገን በማስተሳሰር የምንፈልጋትን አፍሪካ መገንባት አለብን" ብለዋል።

ኪነ-ጥበብ፣ ባህልና ቅርስ የአፍሪካ ህብረት የ2021 ዋነኛ መልእክቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ  የወዳጅነት ፓርክን ጨምሮ የታሪክ አንድነትና ትብብር ምልክት የሆኑ ፕሮጀክቶችን እየገነባች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት 2063 አጀንዳን እውን ለማድረግም መሪዎች በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ትናንት የተጀመረ ሲሆን የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ተወካዮች፣ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብና በአፍሪካ ሕብረት ስር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በመክፈቻ ንግግራቸው የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት አገራት ዘርፈ ብዙ የትብብር ግንኙቶችን መፍጠር እንዳለባቸው መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም