የፍትሃዊነት ባህልን ለዓለም ያስተዋወቀ ግድብ

150

ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለሀገር ልማት ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ሀገራት ጭምር ጠቃሚ ፕሮጀክት መሆኑን የፖለቲካ ተንታኙ አሊይ ቨርጄ ይናገራሉ።

ግድቡ መላው ኢትዮጵያውያንን ለአንድ ዓላማ የሚያሰልፍ፤ለቀጠናው ኢኮኖሚያዊ ትስስርም ጉልህ ሚና የሚጫወት አንድ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት አለ፤እሱም ታላቁ የህዳሴ የሀይል ማመንጫ ግድብ ነው ይላሉ ተንታኙ በጽሁፋቸው፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ አሊይ ቨርዴ ግብጽም ሆነች ሌሎች አገራት የገነቧቸው የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድቦች የቀጠናውን ሀገራት በኢኮኖሚ እና በልማት ለማስተሳሰር በማለም አለመሆኑን ያብራራሉ።

ግብጽ ከአባይ ወንዝ ከምታገኘው የውሃ ሀብት 80 በመቶ የሚሆነውን ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸውን የግብርና ምርቶች ለማምረት የምትጠቀምበት መሆኑን የሚያነሱት ተንታኙ፤ነገር ግን ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ የምትገነባው በዋናነት የኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎቷን ከማሟላት ባሻገር አካባቢውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር በማለም
በመሆኑ ከግብጽ እንደሚለያት ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት እንዲያመነጭ ታቅዶ እየተገነባ ያለውን ግድብ ያለአንዳች ችግር ገንብታ እያጠናቀቀች መሆኑን የገለጹት ጸሃፊው፤የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትም በናይል ወንዝ ላይ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድቦችን መገንባታቸውን አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ ሀገራት ግድቦቹን በሚገነቡበት ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኞቹ የተፋሰሱን ሀገራት አለማማከራቸው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እየገነባች ባለችው ግድብ ላይ ያላቸውን ፍላጎት ኢትዮጵያ ባልፈረመችው የቅኝ ግዛት ስምምነቶች እንድትገዛ ለማስገደድ የሚያደርጉት ጥረት ተገቢነት እንደሌለውም አስገንዝበዋል።

ግብጽ 2 ሺህ 100 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የአስዋን ግድብ በመገንባቷ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሄክታር መሬት ለእርሻ ምቹ እንዲሆን፣ በሚሊየን ለሚቆጠሩ ግብጻውያን የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲያገኙ ማስቻሉን የሚያስታውሱት ተንታኙ መሰል በተፈጥሮ ሀብት የመልማት መብትን ኢትዮጵያ አቅዳ በመተግበሯ ለምን የተቃውሞ ጥያቄ ይነሳል ሲሉም ይጠይቃሉ።

አሁን ላይ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል 47 በመቶ ያህል ህዝብ ብቻ የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ መሆኑን የገለጹት ጸሃፊው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በሚሊየን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ብርሃን እንደሚሰጥ ተስፋ የተጣለበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የሶስቱ ሀገራትን የህዝብ ብዛት እንደዋና የመልማት ግዴታ መለኪያ መሳሪያነት በመጠቀምም የተፈጥሮ ሀብትን በማልማት ሀገራዊ ልማትን ማምጣት ወቅታዊ የኢትዮጵያ መንግስት ውዴታ ሳይሆን
ግዴታ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጸሃፊው የአባይ ወንዝ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል በትብብር ለማደግ እንደመነሻ ሆኖ የሚያገለግል እንጂ የአንድ ሀገር የመኖር እና ያለመኖር የህልውና ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም ብለዋል።

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ኩራት መሆኑን ገልጸው፤ህዝቡም ለአዲሱ መንግስት ድጋፍ መስጠት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

ይህም አሁን በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮችን በጥበብ በማለፍ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ የኢትዮጵያ መጻኢ የልማት ተስፋ እውን እየሆነ ስለመምጣቱ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት የሚገለጸው ግዙፉ ፕሮጀክት በፍትሃዊነት የመጠቀም ባህልን ለዓለም የሚያስተዋውቅ ነው ብለዋል በጽሁፋቸው ፡፡

አልይ ቨርጄ በአሜሪካ ዋሽንግተን ከተማ በሚገኘው የሰላም ኢንስቲትዩት ውስጥ ተጋባዥ ባለሙያ በኋላም በኢንስቲትዩቱ የአፍሪካ ማዕከል ከፍተኛ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።

እኤአ በ2015 በደቡብ ሱዳን የተፈረመው የሰላም ስምምነት ጉዳይን እንዲከታተል የተቋቋመው ኮሚሽን በሰብሳቢነት እንዲሁም በደቡብ ሱዳን በኢጋድ የተመሰረተውን የአደራዳሪዎች ቡድን በዋና አማካሪነት ያገለገሉም ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም