አዲሶቹ የምክር ቤት አባላት የአሸባሪውን ጥፋት ሴራ ለማክሸፍ አበክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል

71

ሠመራ፤ ጥቅምት 4/2014 (ኢዜአ) አዲሶቹ የምክር ቤት አባላት የአሸባሪው ህወሃት የጥፋት ሴራን ለማክሸፍ ህብረተሰቡን በማንቃትና በማስተባበር አበክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ነባሮቹ የምክር ቤት አባላት ገለጹ።
ለአፋር ክልል ነባር የምክር ቤት  አባላት ዛሬ በሠመራ ከተማ  በተዘጋጀ መረሃግብር ሽኝት ተደርጎላቸዋል።
ከነባር አባላቱ  መካከል አቶ መሐመድ ከድር በተለይ  ለኢዜአ እንዳሉት፤ በምክር ቤቱ ቆይታቸው ለክልሉ ህዝብ  ይጠቅማል ብለው  ያመኑባቸውን አጀንዳዎችና የተለያዩ ውሳኔዎች በማሳለፍ ስራ እንዲውሉ የድርሻቸውን ተወጥተዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች ባለፉት ሶስት ዓመታት ምክር ቤቱ ለአርብቶ አደሩ ኑሮ መሻሻል ፋይዳ ያላቸው አረጃጀቶችንና አዋጆችን ማጽደቁን አስታውሰዋል።

 እነዚህ መልካም ጅማሮዎች በአዲሱ ምክር ቤት አባላት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አመልክተዋል።

ለውጡ አልዋጥ ያላቸው  አሸባሪው የህወሃት ቡድንና የውጭ ሃይሎች  ሀገር እስከ ማፍረስ የሚደርሰ  ጥፋት ለመፈጸም እየጣሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሄን የጥፋት ሴራ ለማክሸፍ አዲሶቹ የምክር ቤት አባላት  ህብረተሰቡን  በማንቃትና በማስተባበር አበክረው  መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።  

ሌላው የነበሩ ምክር ቤት አባል አቶ ፈረዴ መኤሚያ በበኩላቸው፤  አዶሶቹ የምክር ቤቱ አባላት ያላቸው የስራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት ተጠቅመው በመጪው ዘመን  ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ  የተሻለ ይሰራሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

በተለይም በእውነተኛ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ሃላፊነታቸውን ከተወጡ ክልሉን ብሎም ሀገርን ወድ ብልጽግና ማማ በማሻገር አዲስ ታሪክ የሚጽፉበት ጊዜ መሆኑን አመልክተዋል።

ለዚህም የምክር ቤቱ አባላት ከጎጠኝነትና ከፋፋይ አጀንዳዎች እራሳቸውን በማራቅ  በሀገር ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመቀልበስ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

''የህወሓት የሽብር ቡድን እኔ ካልመራኋት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አትኖርም "በሚል   ሀገር ለማፍረስ ግልጽ ጦርነት ማወጁን  በማውሳት አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ  ሌላ ተሰናባች  የምክር ቤት አባል አቶ ጀማል መሐመድ ናቸው።

ለዚህም ይረዳው ዘንድ ባለፉት ዓመታት በህዝቦች መካከል መከፋፈልንና አለመተማመንን  ለመፍጠር ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ይህንን የአሸባሪው ቡድን  ሴራ ለማክሸፍ ነባሩ የምክር ቤት አባላት ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ አዲሱ የምክር ቤት አባላት በሀገርና በህዝብ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልስ አበክረው መሰራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን  የሽብር ቡድኑን ሴራ ለማክሸፍ የቆየ አንድነታቸውን ጠብቀው በጋራ መቆም እንዲችሉ  ድጋፍ በመስጠት  የመሪነት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የአዲሱ ምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አስያ ከማል፤ ነባር የምክር ቤት  አባላት ለአፋር ህዝብ ጥቅምና እድገት  አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋቸውን በመግለጽ  ምስጋና አቅርበዋል።

አዲሶቹ የምክር ቤት አባላት ከነባሮቹ  የስራ ልምድ በመውሰድ ጭምር  ለአርብቶ አደሩ የላቀ ተጠቃሚነት፣ ለክልሉ ብሎም  ለሀገር ሰላምና እድገት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አሳስበዋል።
  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም