ኢትዮጵያ አየር መንገድ ከደቡብ አፍሪካው ኤየር ሊንክ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማማ

76

አዲስ አበባ፣ መስከረም 04/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከደቡብ አፍሪካው ኤየር ሊንክ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማማ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ካደረገው ኤየር ሊንክ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡

በሁለቱ አየር መንገዶች መካከል የተደረገው ስምምነት መንገደኞች በነጠላ ትኬት እና በቅናሽ ክፍያ በሁለቱ አየር መንገዶች መዳረሻ ለመጓጓዝ የሚያስችላቸው ነው፡፡

መንገደኞቹ በስምምነቱ በመታገዝ በሁለቱም አየር መንገዶች በኩል ቦታ ማስያዝ የሚያስችላቸው መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ሁለቱ አየር መንገዶች የመሰረቱት አጋርነት መንገደኞች በቀላሉ ወደ መዳረሻቸው እንዲጓዙ ስለሚያስችል በርካታ ደንበኞችን እንደሚስብ ታምኖበታል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያም፤ በጀመርነው ተከታታይና ቁርጠኛ ጥረት በመታገዝ አገልግሎታችንን በአፍሪካ ካለን ሰፊ ትስስር ባሻገር መውሰድ ችለናል አሁንም በአፍሪካ ያለንን ትብብር በማሳደግ ከኤየር ሊንክ ጋር ለመስራት በመቻላችን ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካ የአህጉሪቱን ሰፊ ገበያ የምትመራና በቀጠናው የኢንዱስትሪው ዘርፍ መሪ በመሆኗ ይህ ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ አየር ማረፊያዎች ወደ ውጭና ወደ አገር ውስጥ የሚበሩ መንገደኞችን ወደ አምስቱም ክፍለ አህጉራት በቀላሉ ለማድረስ ያስችለናል ብለዋል፡፡

ስምምነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን መዳረሻዎች በመጠቀም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የአየር መንገዱን ደንበኞች ወደ አፍሪካ አገራትና ወደ ሌሎች የአለም አገራት በቀላሉ የሚደርሱበትን እድል ይፈጥርላቸዋል ተብሏል፡፡

ተጓዥቹ በሁለቱ አየር መንገዶች አመካኝነት በማንኛውም ጊዜ የበረራ ሰነዳቸውንና ሻንጣዎቻቸውን በተገቢው መንገድ ማረጋገጥ ይችላሉ ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም