ዲያስፖራው በጥቁር ገበያ የሚመነዝረው ገንዘብ ኢትዮጵያን ለማዳከም ለሚሰሩ ኃይሎች ድጋፍ እንደሚውል መገንዘብ አለበት

74

አዲስ አበባ፣ መስከረም 04/2014 (ኢዜአ) ዲያስፖራው በጥቁር ገበያ የሚመነዝረው ገንዘብ ኢትዮጵያን ለማዳከም ለሚሰሩ ኃይሎች ድጋፍ እንደሚውል በመገንዘብ "በህጋዊ መንገድ ብቻ መጠቀም ይኖርበታል" ሲሉ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ተግባር ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ተግባር ምክር ቤት አባላት "እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ የፍቅር ጉዞ" በሚል መሪ ሃሳብ ኢትዮጵያን እየጎበኙ ይገኛሉ፡፡

አባላቱ እስካሁን ባለው ሂደት የታላቁ የህዳሴ ግድብ እና የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን የጎበኙ ሲሆን፤ ደም በመለገስ ለኢትዮጵያ ህልውና ዘብ ለቆመው የመከላከያ ሰራዊት አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡

በተጨማሪ በመዲናዋ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተተከሉ ችግኞችን በመንካባከብ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምክር ቤቱ አባላት በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በተለያዩ ጉዳዮች እየደገፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በተለይ ዲያስፖራው በህጋዊ መንገድ ገንዘባቸውን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ አገራቸው የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ እያደረጉ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ነገር ግን የአሸባሪው ህወሃት አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም አንዳንድ ግለሰቦች የጥቁር ገበያ ሰንሰለትን በመጠቀም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አሻጥር ለመስራት ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ነዋሪነታቸው በእንግሊዝ ሀገር የሆነውና የፎቶ ጋዜጠኝነት ባለሙያው አቶ አለባቸው ደሳለኝ  እንደሚሉት፤ ለትንሽ ገንዘብ ጭማሪ ተብሎ የውጭ ገንዘብን በጥቁር ገበያ መመንዘር ኢትዮጵያን የሚወጉ ሃይሎችን ማጠናከር ነው፡፡

በመሆኑም ዲያስፖራው በህጋዊ መንገድ ብቻ ገንዘብ በመላክ ለአገሩ ህልውና ሚናውን መወጣት እንዳለበት ገልጸው፤ ምክር ቤቱ ከዚህ አኳያ "በውጭ አገር ሆነው የጥቁር ገበያ የሚሰሩ አካላትን ለመንግስት በማጋለጥ ኃላፊነቱን ይወጣል ነው" ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ ላይ እየተሰራ ያለውን የኢኮኖሚ ሴራ በመገንዘብ በህጋዊ መንገድ ገንዘብ የሚልኩ የዲያስፖራ አባላት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ነው የገለጹት፡፡

በአሜሪካን አገር የሚኖሩትና የዓለም ባንክ ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ አምሳለ ገሰሰ በበኩላቸው፤ እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ የአሸባሪው ህወሃት አባላት የጥቁር ገበያ ሱቅ ከፍተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እነዚህ አካላት ኢትዮጵያን በኢኮኖሚው ዘርፍ ለማዳከም ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ነገር ግን በርካታ የዲያስፖራ አባላት ይህንን ሴራ ተገንዝበው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

ኢትዮጵያውያንና ትውለደ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በተለያዩ መንገዶች እያገዙ መሆኑን የተናገሩት፤ ደግሞ በአሜሪካን አገር የሚኖሩት አቶ በፍቃዱ ተረፈ ናቸው፡፡

ዲያስፖራው ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ እንዲልክ የሚያበረታቱ ቀልጣፋና ጊዜ ቆጣቢ አሰራሮች መዘርጋት እንዳለባቸውም ነው የገለጹት፡፡

አዲስ የተመሰረተው መንግስት  በዚህ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ዲያስፖራው ከመቼውም ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አንድ ሆኖ እና ተናቦ የሰራ መሆኑንም የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ተግባር ምክር ቤት ከሌሎች መሰል የዲያስፖራ ማህበሮች ጋር በመቀናጀትና ሎቢስቶችን በመቅጠር በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ያልተገቡ ጫናዎችን በመመከት ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝም ነው ያነሱት፡፡

በአገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችና የዲያስፖራው ቅንጅት የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም