በመዲናዋ የሚታየውን የኤች አይቪ ኤድስ የስርጭት ምጣኔ ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተጠቆመ

71
ነሃሴ 11/2010 በአዲስ አበባ አሁን ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የኤች አይቪ ኤድስ የስርጭት ምጣኔ ለመቀነስ የምክርና የምርመራ አገልግሎትን ጨምሮ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ ፡፡ በመዲናዋ የኤች አይቪ ኤድስ የስርጭት ምጣኔ 3 ነጥብ 4 በመቶ ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል:: የኤች አይ ቪ ኤድስ ግንዛቤ የማስጨበጡ ሂደት በፊት ከነበረው እየተቀዛቀዘ መምጣቱንና ህብረተሰቡም ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን የገለጸው የመዲናዋ ወጣት ዳዊት ተስፋዬ ነው፡፡ ለዚህም ህብረተሰቡ በስፋት በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች እየተደረገ ያለውን ነጻ የምክርና የምርመራ አገልግሎት ጨምሮ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታውቋል፡፡ የመተላለፊያ መንገዱ ብዙ መሆኑን በመረዳት ራሱን አውቆ  ጥንቃቄ ለማድረግ በየሶስት ወሩ የኤች አይቪ ኤድስ ምክርና ምርመራ እንደሚያደርግ የተናገረው ወጣቱ ህብረተሰቡ የቫይረሱን አስከፊነት ተረድቶ መታቀብ ፣መወሰንና መጠቀም የሚሉትን ሶስት የመ ህጎች ማክበር እንዳለበትም አስገንዝቧል፡፡ የኮተቤ ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር ወ/ሪት  ህሊና ስጦታው እንዳሉት  ባለፉት አመታት የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራና ግንዛቤ ተቀዛቀዞ የነበረ ቢሆንም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከወጣት ማእከላትና ከእምነት ተቋማት ጋር  በመተባበር በትኩረት ተሰርቷል፡፡ በዚህም 6ሺ 754 ለሚሆኑ ሰዎች ምርመራና ትምህርት በመስጠት 227 ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ተገኝቶባቸዋል፤31 እናቶችም ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ በመሆኑም የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ነጻ የምክርና የምርመራ አገልግሎት ስራው ላይ የበለጠ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የአዲስ አበባ የኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ምክትል ዳይሬክተር ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በበኩላቸው የስርጭት ምጣኔው አምና ከነበረበት 4ነጥብ8 በመቶ ወደ 3 ነጥብ 4 በመቶ ቢወርድም አሁንም ቫይረሱ ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ በ2010 በጀት ዓመት ከእምነት፣ከትምህርት ተቋማትና ከተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች ጋር በመቀናጀት የኤች አይቪ ስርጭትን ለማግታት ለ1ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ራሳቸውን አውቀው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የግንዛቤ ትምህርት ከተሰጣቸው 83 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች የደም ምርመራ አድርገዋል ፡፡ የአመራሩ በቁርጠኝነት አለመንቀሳቀስ፣የአጋላጭ ጉዳዮች መብዛትና የባሪ ለውጥ ለማምጣት ብዙ ጊዜ መጠየቁ አሁንም ስራውን ፈታኝ እንዳደረገው  በጥናት መለየቱን  ሲስተር ፈለቀች ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ለወጣቶችና ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች  የባህሪ ለውጥ የሚያመጣ የግንዛቤ ትምህርት በትኩረት እየተሰራ እንዳለም ገልጸዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የስርጭት ምጣኔው ጋምቤላ ክልል በ4 በመቶ ከፍተኛውን ደረጃ ሲይዝ፣ አዲስ አበባ በ3ነጥብ4 በመቶ ይከተለዋል፤ አነስተኛ የስርጭት ምጣኔ የሚታየውም በሶማሌ ክልል መሆኑ ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ከ6 መቶ ሺ በላይ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ከፌደራል ኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም