የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የኮሮና ተፅዕኖን መቀነስ በሚቻልበት መንገድ እንዲወያዩ ተጠየቀ

60

ጥቅምት 4/2014(ኢዜአ) የአፍሪካ ህብረት የአስፈፃሚ ምክርቤት ተሳታፊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የኮሮና ተፅዕኖን መቀነስ በሚቻልበት እና የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ አፍሪካ ሲዲሲን በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ በሚገባበት መንገድ እንዲወያዩ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት ዛሬ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ህብረት መደበኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የአስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ነው።የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረረሽኝ በአህጉሪቷ ላይ ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን እንደፈጠረ ለስብሰባው ተሳታፊዎች አስረድተዋል።

በመሆኑም የአስፈፃሚ ምክርቤት ተሳታፊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የኮሮና ተፅዕኖን መቀነስ በሚቻልበት መንገድ ላይ ያተኮረ ውይይት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።ከዚህ በተጨማሪ የህብረቱ 2022 በጀት ላይም ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርሰቶፌ ሉቱንዱላ በበኩላቸው የአስፈፃሚ ምክርቤቱ የመወያያ አጀንዳዎችን ዘርዝረዋል ።

የኮሮና ቫይረስ ወረረሽኝ ተፅዕኖ፣የአፍሪካ ሲዲሲ ወደ ስራ የማስገባት ሒደት፣አፍሪካ ህብረትን ይበልጥ ማጠናከር ፣ሁለት ኮሚሽነሮችን እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችን መመረጥ ተጠቃሽ ናቸው።ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ስብሰባው በአካል ሲደረግ የአሁኑ የመጀመሪያው መሆኑን ከውጭ ጉዳይ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም