የመልካም አስተዳደር ችግርሮች እንዲፈቱላቸው በጋምቤላ ከተማ ወጣቶች ጠየቁ

65
ጋምቤላ ነሓሴ 11/2010 የልማት ተጠቃሚነታቸውን እየተፈታተኑ ያሉት የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱላቸው የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች ጠየቁ። የከተማዋ ወጣቶች እንደ ሀገር እየመጣ ባለው ለውጥና በክልሉ በሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂደዋል። ከወይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ኡሞድ ኡቻላ በሰጡት አስተያየት በክልሉ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ሊፈታ ባለመቻሉ በተለይም ወጣቱን የልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን እያደረገው መሆኑን ተናግሯል። የመጀመሪያ ዲግሪ ይዘው  የስራ እድል ማግኘት ባለመቻላቸው ተቸግረው እንዳሉ ጠቁሞ የሚፈጠሩ የስራ እድሎችም ለባለስጣን ዘመድና ባለሀብት እየተሰጠ በእኩልነት ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ገልጿል። እንደ ሀገር እየመጣ  ያለው ለውጥና እየተተገበረ ያለው ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር በክልሉ ተግባራዊ ባለመደረጉ ችግሮች እየተፈቱ አለመሆናቸውን የተናገረው ደግሞ ሌላው ወጣት ጋትቤል ፖል ነው። ወጣት ሮድ ጀምስ በክልሉ እንደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢ ወጣቶች ተጠቃሚ ባይሆኑም ሰላም ካለ የሚፈልጉት ተጠቃሚነት በሂደት እንደሚሳካ በማመን የአካባቢያቸውን ጸጥታ በማስከበር የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ የክልሉ መንግስት በወረቀት ላይ ከማስቀመጥ ባለፈ እንደ ሀገረ የመጣውን ለውጥ ተግባራዊ በማድረግ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባም ጠቁሟል። ሌላው ተሳታፊ ወጣት ኡቦንግ ኡጉታ እንደ ሀገር እየመጣ ያለውን ሁሉንም ያቀፈና  ጥላቻን የሻረው ለውጥ በክልሉ ተግባራዊ ሆኖ ወጣቶቹ የልማቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ አመልክቷል። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ በክልሉ ጎሳን መሰረት ያደረገ የስልጣን አወቀቀር፣ የስራ ቅጥርና  የስራ እድል ፈጠራ ዋነኛ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ስለሆኑ በፍጥነት ሊታረሙ ይገባል። ያለ ሰላም የሚመኙት የልማት፣ የዴሞክራሲና የአብሮነት እሴቶችን ማግኘት ስለማይቻል የአካባቢያቸውን ጸጥታ ለማስከበር እንደሚጥሩም ተናግረዋል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳዳር አቶ ሰናይ አኩዎር "በወጣቶቹ የተነሱትን የስራ እድል ፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተያዘው የበጀት ዓመት ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግስት በትኩረት ይሰራል" ብለዋል። ወጣቶቹ ብሄረንና ጎሳን መሰረት ያደረገ የአመራር ምደባ ቀርቶ ብቃትን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆን እንዳለበት ያቀረቡት ጥያቄ አግባበነት ያለው መሆኑንና እንደ ድርጅትም ታምኖበት ወደ ተባለው አሰራር መገባቱን አመልክተዋል። ወጣቱቹ በሚፈልጉት ደረጃ የስራ አድል መፍጠር ያልተቻለው ክልሉ ባለው የበጀት እጥረት መሆኑን ጠቁመው በበጀት ዓመቱ አብዛኛዎቹን ወጣቶች በተቻለ አቅም የስራ እድል ተጠቃሚ ለማደረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። የክልሉ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም ነቆ በመጠበቅ ረገድ ለሳዩትን ቁርጠኝነት አመስግናው ወደፊትም ይህንኑ ተግባር አጠናከረው እንዲቀጥሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አሳሰበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም