በምዕራብ ጎንደር ዞን በ130 ሺህ ሄክታር መሬት የለማ ሰሊጥ እየተሰበሰበ ነው

172

መተማ፤ ጥቅምት 4/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ለውጭ ገበያ የሚቀርብ በ130 ሺህ ሄክታር መሬት የለማ ሰሊጥ በመሰብሰብ ላይ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
 እየተሰበሰበ ያለው የሰሊጥ ምርት ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን በ2013/14 ምርት ዘመን በባለሃብቶችና አርሶ አደሮች የለማው  ነው።

በዞኑ በስፋት የሚመረተውና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኘው ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት በፍጥነት እየተሰበሰበ መሆኑን በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በሰሊጥ ሰብል ከለማው መሬት ውስጥ 50 ሺህ ሄክታር በእርሻ ኢንቨስትመንት በተሰማሩ ባለሃብቶች የለማ፤ ቀሪው ደግሞ በአርሶ አደሮች መልማቱን ገልጸዋል።

ባለሙያው እንዳሉት፤ እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ በ55 ሺህ ሄክታር መሬት የለማ ሰሊጥ ማሳ መሰብሰቡን ጠቅሰው፤እስከዚህ ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ከማሳ ላይ ለማንሳት እየተሰራ ነው።

ሰሞኑን እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሰሊጥ ሰብል ላይ  ብክነት ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ጊዜውን ተጠቅመው እንዲሰበስቡ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

ከለማው መሬትም አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለሙያው አስታውቀዋል።

በመተማ ወረዳ የሽመለ ጋራ ቀበሌ  አርሶ አደር አዳነ ምስጋናው እንደተናገሩት፤ በሰሊጥ ከሸፈኑት 5 ሄክታር መሬት ውስጥ 2 ሄክታሩን መሰብሰብ ችለዋል።

''ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በጣም አስቸግሮናል'' ያሉት አርሶ አደሩ ፤ ቀሪውን የሰሊጥ ሰብል ጉዳት ሳይደርስ ለመሰብሰብ የጉልበት ሰራተኛን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸውን በመጠቀም እየሰበሰቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ካለሙት መሬት 22 ኩንታል ሰሊጥ ምርት አግኝተው በነበረው የተሻለ የገበያ ሁኔታ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰው፤ አሁን ያለውን የገበያ ሁኔታም መልካም ነው ብለዋል።

በመተማ ወረዳ ደለሎ የእርሻ ልማት በ40 ሄክታር መሬት ላይ ሰሊጥ ማልማታቸውንና ባለፉት ቀናት 25 ሄክታሩን ብክነት ሳይደርስ መሰብሰብ እንደቻሉ የገለጹት ደግሞ አቶ ጀጃው አብርሃ ናቸው።

''የጉልበት ሰራተኛ እጥረትና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መጣል ችግር እንደፈጠረ ጠቅሰው፤ ችግሩን ተቋቁመው የቤተሰቦቻቸውን ጉልበትና አነስተኛ ቁጥር ያለው የጉልበት ሰራተኛ በመጠቀም እየሰበሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በሰሊጥ ከተሸፈነው መሬት ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ምርት በመሰብሰብ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደተቻለ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም