የምገባ ፕሮግራም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ አግዟል

67
ጎንደር ነሀሴ 11/2010 በማእከላዊ ጎንደር ሶስት ወረዳዎች የተካሄደው የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ከ10ሺ በላይ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ አስተዋጽኦ ማድረጉን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡ ህብረተሰቡ የጉልበት የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ጭምር በማድረግ ለምገባ ፕሮግራሙ መሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ ለኢዜአ እንደተናገሩት በ2010 የትምህርት ዘመን በዞኑ በ113 የቅድመና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡ በምስራቅ በለሳ በኪንፋዝ በገላና በወገራ ወረዳዎች በትምህርት ዘመኑ በተካሄደው የምገባ ፕሮግራም ከ57ሺ በላይ ተማሪዎችን የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ የምገባ ፕሮግራሙ በትምህርት ቤቶቹ መሰጠቱ በአንደኛ ወሰነ ትምህርት ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ከ10ሺ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ በማድረግ አዎንታዊ ውጤት መመዝገቡን ሃላፊው ገልጸዋል፡፡ ፕሮግራሙ በተጨማሪም በተማሪዎች ላይ ይታይ የነበረውን አልፎ አልፎ የመቅረትና የማርፈድ ምጣኔን በመቀነስ ለትምህርት ዘመኑ እቅድ መሳካት አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ አልሚ ንጥረ ነገሮች በማካተት ምግብ ተዘጋጅቶ በቁርስና በምሳ ሰአት ተማሪዎቹ እንዲመገቡ መደረጉ ለተማሪዎቹ አእምሮአዊ እድገትና የትምህርት አቀባበል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ መንግስት ለምግባ ፕሮግራሙ ከአራት ሺ ኩንታል በላይ የአልሚ ምግብ ይዘት ያለው ዱቄት በማቅረብ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡ የምገባ ፕሮግራሙ በ2011 የትምህርት ዘመን ቀጣይነት እንደሚኖረው የተናገሩት ኃላፊው በፕሮግራሙ የሚካተቱ ትምህርት ቤቶችን በጥናት የመለየት ስራ በትምህርት ዘመኑ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡ ''ፕሮግራሙ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የፈረቃ ትምህርትን ወደ ሙሉቀን ትምህርት ለመቀየር አስችሏል'' ያሉት ደግሞ የምስራቅ በለሳ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይደግ ልጃለም ናቸው፡፡ በወረዳው በ2010 የትምህርት ዘመን ከ20ሺ በላይ ተማሪዎችን የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ያሉት ሃላፊው ከ3ሺ በላይ አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎችንም ወደ ትምህርት ገበታ በማምጣት በኩል ፕሮግራሙ እገዛ አድርጓል፡፡ በኪንፋዝ በገላ ወረዳ የጭቅቂ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተሾመ መርሻ ''የአካባቢው ነዋሪ በእርዳታ እህል ኑሮውን የሚገፋ በመሆኑ የምገባ ፕሮግራሙ መጀመር  ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት እንድንልክ አግዟል'' ብለዋል፡፡ ''እኔም ሆንኩ የአካባቢው ህብረተሰብ ለምገባ ፕሮግራሙ በወር 10 ብር በማዋጣት የቀን ሰራተኛ ወጪ በመሸፍንና የማገዶ እንጨት በማቅረብ ድጋፍ አድርገናል'' ያሉት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የስላሬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገዳሙ መንገሻ ናቸው፡፡ በማእከላዊ ጎንደር ዞን የ2010 የትምህርት ዘመን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የቅድመና የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸው መከታተላቸውን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም