መንግስት ከወደቅኩበት ስላነሳኝ ተደስቻለሁ

77

ሐረር፤ ጥቅምት 3/ 2014 (ኢዜአ )መንግስት ከወደቅኩበት ስላነሳኝ ተደስቻለሁ ይላሉ ወይዘሮ አሻ ሙመድ።

ወይዘሮ አሻ  በሚኖሩበት ሐረሪ ክልል ኤረር ወረዳ  የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  አስገንብቶ ዛሬ ካስረከባቸው መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚ አቅመ ደካማ ቤተሰቦች መካከል አንዷ ናቸው።

''መንግስት ከወደቅኩበት ስላነሳኝ ተደስቻለሁ፤አሁንም ወደፊትም ሀገሬን እና ህዝቤን ፈጣሪ ይጠብቅልኝ” ሲሉ  ወይዘሮ አሻ የመኖሪያ ቤቱን ቁልፍ በተረከቡበት ወቅት  ገልጸዋል።

በተገነባላቸው መኖሪያ ቤት ውስጥም ፈጣሪያቸውን በማመስገን  ከቤተሰቦቻቸው ጋር በደስታ እንደሚኖሩበት ነው  የተናገሩት።

ቀደም ሲል ከምኖርበት  ደሳሳ እና ጨለማ ቤት አውጥቶኝ ብርሃን ወዳለው መኖሪያ ቤት እንድኖር ስላደረገኝ ለመንግስት ምስጋና   አቀርባለሁ ያሉት ደግሞ  ሌላዋ አቅመ ደካማ ወይዘሮ  ሂንዲ አብዶሽ ናቸው።

በዚህም ድጋፍ የራሴንና የልጆቼን ህይወት ለመቀየር ጠንክሬ እሰራለሁ ብለዋል።

በኤረር ወረዳ  ወልዲያ እና ሃዋዩ ቀበሌ ገበሬ ማህበራት  የተገነቡ መኖሪያ ቤት ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ያስረከቡት የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አዲስዓለም በዛብህ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ ናቸው።

አፈ ጉባዔዋ በወቅቱ እንደተናገሩት በክልሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ስድስት  ተጠሪ ተቋማት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ 14 መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው  ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ተከፋፍለዋል።

ዛሬ ደግሞ  በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  የተገነቡት  መኖሪያ ቤት የአቅመ ደካሞችን ችግር ስለሚያቃልል ለተቋሙ ምስጋና አቅርበዋል።

የመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ እንዲፋጠንና በወቅቱ ለነዋሪዎቹ እንዲደርስ በማድረግ በኩል የወረዳው አስተዳደር ፣ የአካባቢ ወጣቶችና ማህበረሰቡ ላደረጉት ትብብርና ድጋፍም አፈ ጉባኤዋ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች  በቀጣይም እንዲጠናከሩም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ተነሳሽነት በመውሰድና ካለው በጀት ላይ በመቀነስ አቅመ ደካማ ቤተሰቦች መጠለያ እንዲያገኙ የበኩሉን ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል።

መልካም ስራ እየተስፋፋ የሚሄድና የሚያድግ እንጂ የሚቆም አይደለም ያሉት አቶ ተፈራ፤ በቀጣይም ተቋሙ የጀመረው የበጎ አድራጎት ሥራ እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ኢዜአ ለአቅመ ደካማዎች  ቤቶችን  ሰርቶ በማስረከቡ ደስታቸውን በባህላዊ ጭፈራና ውዝዋዜ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም