ከ600 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የኮንትሮባንድ እቃ በቁጥጥር ስር ዋለ

79

ዲላ፤ ጥቅምት 3/2014 (ኢዜአ) በጭነት ተሽከርካሪ ሲዘዋወር የነበረ ከ600 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የኮንትሮባንድ እቃ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ የጪጩ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስታወቀ።

የኮንትሮባንድ እቃው በቁጥጥር ስር የዋለው መነሻውን ቡሌ ሆራ አድርጎ ወደ ዲላ ሲጓጓዝ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-16051 አ.አ  "ኤፍ ኤስ ኤር " የጭነት ተሽከርካሪ ላይ መሆኑን የመቆጣጠሪያ ጣቢያው አስተባባሪ ኮማንደር ጫላ ቡልቻ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም  ከ5 ሺህ 400 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን 60 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅ  መገኘቱን አስታውቀዋል።

አሽከርካሪው ለጊዜው ከአካባቢው ሸሽቶ ቢያመልጥም  በቁጥጥር ስር ለማዋል  ክትትል እየተደረገበት   መሆኑን ገልጸዋል።

ጣቢያው ከዚህ ቀደም ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባደረገው የቁጥጥር ስራ  በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ100  በላይ ኮንትሮባንድ አዘዋዋሪ አሽከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም