የአካባቢውን ሰላምና ልማት ለመጠበቅ ጠንክረው እንደሚሰሩ የድሬዳዋ የእስልምና እምነት አባቶች ተናገሩ

64
ድሬዳዋ ነሃሴ 11/2010 በድሬዳዋ አስተዳደር አስተማማኝ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰሩ የአስተዳደሩ የእስልምና እምነት አባቶችና ሼኮች ተናገሩ፡፡ በድሬዳዋ የሚገኙ ኡለማዎች፣ ሼኮች፣ ኢማሞችና የኃይማኖት አባቶች  በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ትናንት ባካሄዱት ውይይት ብሔርንና ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በወጣቶች መካከል ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትን አውግዘዋል፡፡ ወጣቶችን ርስ በርስ በማጋጨት የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት ለማደፍረስ ሌት ተቀን የሚሰሩ አካላትን ለህግ-አሳልፈው በመስጠት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ገልፀዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ወጣቶች ተቧድነው ርስ በርስ ግጭት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ማስተዋላቸውን ጠቅሰው እነዚህን  ወጣቶች በመምከርና በመገሰጽ ለአካባቢያቸው ሰላምና ልማት እንዲተጉ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡ የህብረተሰቡ ባህላዊ መሪ የሆኑት አባገዳዎችና ኡጋዞችም ወጣቶችን በማሰባሰብ፣ በመምከርና በማስታረቅ ለሀገር ሰላምና ዕድገት ተቀናጅተው ለመስራት የጀመሩትን ስራ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡ የውይይት መድረኩን የመሩት ሼህ አሚን ኢብሮ እንደገለፁት ''ቤተሰብ ወደ ጥፋት የሚሄዱ ልጆችን የመገሰጽና የኃይማኖቱ አባቶች ደግሞ ሊቀጣጠል  ባሰበው እሳት ላይ  ውሃ የመርጨት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል'' ብለዋል፡፡ በተጨማሪም  የእምነቱ መሪዎች በቅርቡ በተፈጠረው ጥፋት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና ወደ ሌላ አካባቢ የተሰደዱ ወገኖችን ወደ ቀያቸው የመመለስ እና የመደገፍ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳሰበዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ሼህ አሊ አህመድ በቅርቡ በሰፈራቸው የተፈጠረው  ሁከት እንዳይሰፋና ተጨማሪ ቀውስ እንዳይፈጥር የእምነቱ አባቶች ሰላምን ለማውረድ ከፍተኛ ሥራ መስራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ''ለአካባቢያችን ሰላም መረጋገጥ እየሰራን  ነው፤ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እያደረግን ነው'' ብለዋል፡፡ ''ወጥቶ ለመግባትና ኃይማኖታዊ ተልዕኮን ለመፈጸም ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ሰላምን ለመጠበቅ ሁላችንም እንረባረባለን'' ያሉት ደግሞ መሐመድ ሁሴን  ናቸው፡፡ በተለይ  የድሬዳዋ ህብረተሰብ ያዳበረውን የመረዳዳትና የመተሳሰብ  መልካም እሴት አጠናክሮ እንዲቀጥል ተግተው እንደሚሰሩ  ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፀሐፊ ዑስታዝ እዮብ ሐሰን የተካሄደው ውይይት የአካባቢን ሰላምና ዕድገት ለመጠበቅ የእምነቱ መሪዎች የድርሻቸውን ይበልጥ ለመወጣት እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም