በደቡብ ክልል የጥፋት ተላላኪዎችን ሴራ በማክሸፍ ውጤታማ ስራ ተከናወነ

60

አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 3/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የአሸባሪው ህወሃት ተላላኪዎችን የጥፋት ሴራ ለማክሸፍ የተደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በኮሚሽኑ የ2013 ዓ.ም. የእቅድ አፈፃጸምና የተያዘው የስራ ዘመን ዕቅድ  ዙሪያ የመከረ ጉባኤ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ነቢዩ ኢሳያስ እንደገለጹት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎች በክልሉ በፈጠሩት ችግር በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

በህቡዕ የተደራጁ ሃይሎች በህገ-ወጥ የጦር መሣሪያና ኮንትሮባንድ ንግድ በመጠመድ የህዝቡን ሰላም እያሳጡ  እኩይ ተግባር መፈጸማቸውንም አውስተዋል።

በተለይ ሸካ፣ ሃዲያ፣ ጉራጌ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ ዞኖችና አሌ ልዩ ወረዳ  እና ሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች የሽብር ቡድኑ የጥፋት ተልዕኮ ኢላማ እንደነበሩ አመልክተዋል።

ይህንን እኩይ እንቅስቃሴ ለመግታት ባለፈው ዓመት ብቻ በተደረገው እንቅስቃሴ ከ300 በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች  በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ኮሚሽነሩ  ተናግረዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም 211 ተጠርጣሪዎች ተይዘው ለህግ መቅረባቸውን  ገልጸው፤  ግምታቸው 38 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መቆጣጠር መቻሉንም ጠቅሰዋል።

ከሐሰተኛ የብር ኖት እና አደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋርም 190 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው አስታውቀዋል።

ይህንን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ መግታትን ጨምሮ የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ የመደበኛ፣ የልዩ ኃይልና የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም የሚሊሻ አካላት ሚና የጎላ እንደነበር  ተናግረዋል።

በተለይ ስድስተኛው ጠቅላላ  ምርጫና የደቡብ ምዕራብ ዞኖች ህዝበ ውሳኔ ካለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ  ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል።

''ይህ ለውጥ የመጣው የሰላም ባለቤት የሆነው ህዝብ ከፀጥታ አካሉ በቅንጅት በመስራቱ እንደሆነ  ነው ኮሚሽነር ነቢዩ  ያመለከቱት።

የሽብር ቡድኑ በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር  ለመፍታት ከኦሮሚያና ጋምቤላ ክልሎች የጋራ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።

የቤንች ሼኮ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ምናሉ ታደሰ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሽብር ቡድኑ ዞኑን  ኢላማ አድርጎ  የህዝቡን ሰላም በማደፍረስ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

የፀጥታ መዋቅሩ ስራ ካለህዝብ ተሳትፎ ሰላም ማረጋገጥ አይችልም'' ያሉት ምክትል ኮማንደር ምናሉ፤ በአካባቢ የነበረው የፀጥታ ችግር  ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራት መቀነስ መቻሉን  አስረድተዋል።

የህዝቡ ሁሉን አቀፍ አስተዋጽኦ የደቡብ ምዕራብ ዞኖች በክልል የመደራጀት ጥያቄ በሰላም እንዲጠናቀቅ ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በአደረጃጀት መዋቅር ጥያቄ ሽፋን ፀረ-ሰላም ሃይሎች ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ቢንቀሳቀሱም በማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዘርፍ በተከናወነው ስራ ዞኑን የሰላም ቀጠና ማድረግ መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ጎአ ኩሳ ናቸው።

የፀረ-ሰላም ሃይሎችን እንቅስቃሴ ለመመከት በሚደረገው ጥረት የህዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አመልክተዋል።

የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጡ ረገድ በክልሉ ካሉ ዞኖች መካከል የወላይታ ዞን ግንባር ቀደም አፈጻጸም ማስመዝገቡን በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

በደቡብ ክልል ከሚገኙ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የፀጥታ አካላት  በጉባኤው መድረክ ተሳትፈዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም