የአገራዊ ለውጡ ባለቤትና ጠባቂ ህዝብ እንደሆነ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ

109
አዲስ አባባ ነሀሴ 11/2010 ኢትዮጵያ ለተሻለ ዕድገትና ብልጽግና ሁሉን አቀፍ በሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ እየተካሄደ ያለው አገራዊ ለውጥ ባለቤትና ጠባቂም ህዝብ እንደሆነ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ጽህፈት ቤቱ በሳምንታዊ የአቋም መግለጫው እንዳስታወቀው ፤ መንግስትና ህዝብ የሚፈለገውን ዕድገትና ብልጽግና ለማምጣት በጊዜ የለኝም መንፈስ እየተረባረቡ ይገኛሉ። ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች የህግ የበላይነትን የሚጻረሩ አንዳንድ ተግባራትና ግጭቶች እየታዩ እንደሆነ አመልክቷል። እነዚህን ጤናማ ያልሆኑ ተግባራት የአገሪቱን ገጽታ የማያሳዩ ከመሆናቸውም በላይ የየትኛውንም ብሄር፣ ሐይማኖትና ህዝብ እንደማይወክሉ አስታውቋል። ተግባራቶቹ ኢትዮጵያውያን ከሚታወቁባቸው ድንቅ እሴቶች በተጻራሪ የሚፈጸሙ በመሆኑ መላው ህዝብና መንግሥት በጥብቅ የሚያወግዛቸው ተግባራት እንደሆኑም ገልጿል። የሁሉም ኢትዮጵያውያን ፍላጎት በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ  እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለፍሬ በማብቃት የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የነጻነት፣ የእኩልነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል። በአሁኑ ወቅት መንግሥት እነዚህን የህዝብ ፍላጎቶች ለማሳካት በሥራ በተጠመደበት ጊዜ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚፈጸሙ አፍራሽ ተግባራት የተጀመረውን አገራዊ ሪፎርም ለማፋጠን የሚገፋፋ እንጂ ወደ ኋላ ሊጎትት እንደማይችል የመንግሥት እምነት እንደሆነ አስታውቋል። የአቋም መግለጫው መግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል የተሻለች አገር ለመፍጠር ቅድሚያ ለሰላማችን እና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ በጋራ ዘብ ልንቆም ይገባል አገራችን ኢትዮጵያ ለተሻለ ዕድገት እና ብልጽግና ሁሉን አቀፍ በሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች፡፡ እየተካሄደ ያለው አገራዊ ለውጥ ባለቤትም፣ ጠባቂም ህዝቡ ነው፡፡ መንግስት እና ህዝብ ወደፊት ልንደርስበት የምንፈልገውን ዕድገት እና ብልጽግና ለማምጣት በጊዜ የለኝም መንፈስ እየተረባረቡ ባሉበት በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ የአገራችን ክፍሎች የህግ የበላይነትን የሚጻረሩ አንዳንድ ተግባራት፣ አልፎ አልፎም ግጭቶች ብቅ ጥልቅ ሲሉ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ጤናማ ያልሆኑ ተግባራት አጠቃላዩን የአገራችንን ገጽታ የማያሳዩ ከመሆናቸውም በላይ የትም ይፈጸሙ እንጂ የትኛውንም ብሄር፣ ኃይማኖት ወይም ህዝብ የማይወክሉ ናቸው። ኢትዮጵያውያን ከሚታወቁባቸው ድንቅ እሴቶች በተጻራሪ የሚፈጸሙ በመሆናቸውም መላው የኢትዮጵያ ህዝብና የኢፌዴሪ መንግስት በጥብቅ የሚያወግዟቸው ተግባራት ናቸው። ዛሬ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ፍላጎት በአገራችን አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ፣  እየተካሄደ ያለውን አገራዊ ለውጥ ለፍሬ ማብቃት እና በዚህም ሲያነሳቸው የነበሩ የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የነጻነት፣ የዕኩልነት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተፈተውለት ማዬት ነው። ይህንኑ ፍላጎታችንን ለማሳካት በተጠመድንበት በአሁኑ ወቅት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚፈጸሙ አፍራሽ ተግባራት የጀመርነውን አገራዊ ሪፎርም እንድናፋጥን የሚገፋፉን እንጂ ወደኋላ ሊጎትቱን እንደማይችሉ የኢፌዴሪ መንግሥት ያምናል፡፡ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ማሰባሰብ የቻለውን አገራዊ ለውጥ ለማፋጠን እና ለፍሬ ለማብቃት ሰላምን እና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን መገንዘብ ያሻል። በመሆኑም መላው ሕዝባችን በተለይም ወጣቶች፣ ከተያያዝነው የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመደመር ጉዞ አንፃር ጤናማ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችና ግጭቶች ሊያስከትሉት የሚችለውን ተጽዕኖ ከወዲሁ በመረዳት እንደተለመደው ለሰላም እና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ የኢፌዴሪ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም