ለአርሶ አደሮች የተሰጠው ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ተጠቃሚነታቸውን በዘላቂነት ለማስከበር አስችሏል

96

ባህር ዳር ፤ ጥቅምት 2/2014 (ኢዜአ) ለአማራ ክልል አርሶ አደሮች የተሰጠው ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በዘላቂነት ከማስከበሩም በላይ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት እንዳስቻለ የክልሉ መሬት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር ሥርዓት ግንባታን ሙሉ በሙሉ ለተገበሩ 40 ወረዳዎች ዕውቅና ተሰጥቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ለኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ልማት መሰረት የሆነውን መሬት በአግባቡ ጠብቆና ተንከባክቦ ማልማት ያስፈልጋል።

በክልሉ 95 ወረዳዎች ከ9 ሚሊዮን የሚበልጡ የእርሻ ማሳዎችን በመለካትና ወደ ዲጂታል በመቀየር ወደ ዳታ ቤዝ መግባታቸውንም አስረድተዋል።

ከዚህም ባለፉት አራት ዓመታት ከ 1ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ለተያዙ 7 ሚሊዮን ማሳዎች የሁለተኛ ደረጃ ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተሰጥቷል ነው ያሉት።

ይህም የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱን ለላቀ ልማት ለማዋልና የአርሶ አደሩን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም ገቢን ለማሳደግና ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት እንዳስቻለ አስታውቀዋል።

ለአብነትም በሰሜን ሸዋ ዞን ብቻ በዓመት ከመሬት ገቢ ግብር የሚሰበሰበውን 23 ሚሊዮን ብር ወደ 53 ሚሊዮን ማሳደጉን ጠቅሰዋል።

በቢሮው የመሬት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ታከለ ሃብቴ በበኩላቸው፤ የመሬት ሃብት አያያዙን ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ በመቀየር በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ከሚገኙ 4 ሚሊዮን 369 ሺህ ባለይዞታ አርሶ አደሮች ማሳ 40 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ማሳቸውን በዘመናዊ የመሬት መረጃ አስተዳደር ሥርዓት በማስገባት ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ ነው ብለዋል።

የአርሶ አደሩን የመጠቀም መብት በማረጋገጥ የመልካም አስተዳደር ችግር ከመፍታት ባለፈ ለመሬታቸው በተሰጣቸው ካርታ ብድር ማግኘት እንዳስቻላቸውም አስረድተዋል።

በዚህም ከ10 ሺህ 500 የሚበልጡ አርሶ አደሮች ከ360 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ወስደው ተጨማሪ ሃብት በሚያመነጩ ሥራዎች በመሰማራት ኑሯቸውን ማሻሻላቸውን ተናግረዋል።

ለዕውቅና የበቃነው በ2013 በጀት ዓመት በዞኑ ካሉ 22 ወረዳዎች 17ቱ በተቀናጀ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ በመቻሉ ነው ያሉት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን የገጠር መሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ባዩ ከበደ ናቸው።

ይህም ከመሬት ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከ99 በመቶ በላይ ማስቀረቱንና በቀጣይም ሌሎች ወረዳዎችን የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

በተዘጋጀው የዕውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት 40 ወረዳዎች የምስክር ወረቀት፣ ሽልማትና ሌሎች ማበረታቻዎች ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም