በድሬዳዋ የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት /አተት/ በሽታ ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው

112
ድሬዳዋ ነሀሴ 11/2010 በድሬዳዋ የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት /አተት/ በሽታ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡ በቢሮው የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ሂደት ባለቤት አቶ አብዶ ሙሜ ለኢዜአ እንደተናገሩት የአተት በሽታ በከተማው ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ተከስቷል፡፡ እስካሁን ምልክቱ የተገኘባቸው 70 ሰዎች በ5 ዋና ዋና የጤና ተቋማት ተወስደው ተገቢው ህክምና እየተሰጣቸው ሲሆን ግማሽ ያህሉ ተገቢውን ህክምና አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ አብዶ ገለጻ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ በክረምት ወራት እንደሚከሰት ታሳቢ በማድረግ ቀደም ሲል የተሰራው ሰፊ የመከላከል ስራ በሽታው በፍጥነት እንዳይዛመት አግዟል፡፡ ህመሙ በተከሰተበት አካባቢ ቫክቴሪያውን በኬሚካል የማጥፋት ስራ መሰራቱን ጠቁመው ከህሙማን ጋር ንክኪ በፈጠሩ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶችም ተመሳሳይ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡ በንጽህና ጉድለት ሳቢያ ከሰው ወደ ሰው በቫክቴሪያ  አማካይነት በፍጥነት የሚተላለፈውን በሽታ ለመከላከል ነዋሪው የግሉንና የአካባቢውን  ንጽህና በአግባቡ በመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ለህሙማን ከተዘጋጁት የጤና ተቋማት አንዱ የሳቢያን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሚኪያስ ሰለሞን በበኩላቸው ካለፈው እሁድ ጀምሮ ለህሙማኑ በተዘጋጀው ሥፍራ ህክምና መስጠት መጀመሩንና የተሸላቸው ወደ የቤታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ በአሁን ሰዓት በሆስፒታሉ አራት ህሙማን ብቻ በመታከም ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም