ሁሉም ዜጋ ለሠንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር በመስጠት ለአዲስ ምዕራፍ ጉዞ ስኬት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

66

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 1/2014 (ኢዜአ) ሁሉም ዜጋ ለሠንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብርና ፍቅር በመስጠት ለአዲስ ምዕራፍ ጉዞ ስኬታማነት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ  በደቡብ ክልል ሲከበር የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ ፤  ሰንደቅ ዓላማ  የሀገራዊ አንድነት፣ ነጻነትና  የማንነት ክብር  መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ለሀገርና ሰንደቅ ዓላማ ክብር ጸንቶ በመቆም መስዋዕትነትን መክፈል የክብሮች ሁሉ የላቀው ሀገራዊ ክብር  መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሁሉም ዜጋ ለሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብርና ፍቅር በመስጠት ለአዲስ ምዕራፍ ጊዜ ስኬታማነት  የድርሻውን እንዲወጣ  ጥሪ አቅርበዋል።

''የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን  ለሰንደቃችን ክብር ከፍተኛ ተጋድሎ እየተደረገ ባለበት ወቅት መከበሩ ልዩ ትርጉም አለው'' ብለዋል።

ለሰንደቅ ዓላማ የሚሰጠው ክብር ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት የጋራ መግባባት በመፍጠር ለአዲሱ ምዕራፍ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አስገንዘበዋል።

ሁሉም ሰራተኞች ለሰንደቅ ዓላማ ያላቸውን ክብር በየተሰማሩበት የሙያ መሰክ ስኬታማ በመሆን በተግባር እንዲያሳዩ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አጎ ቃል አስገብተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ሰይፉ ቦጋለ ፤ሰንደቅ ዓላማ የሀገር የነጻነት፣ ድልና አንድነት ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ለመፈታተን የሚደረጉ ጫናዎችን በማክሸፍ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።           

''ሀገርን  ከተረጂነት  ማላቀቅ የዚህ ትውልድ አደራ መሆን አለበት'' ያሉት  አቶ ሰይፉ፤ ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የሙያ ዘርፍ በርትቶ በመስራት ሀገርን ለመበተን ሌት ተቀን የሚደክሙ አንዳንድ ምዕራባዊያ ሀገራትን  ማሳፈር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ባልደረባ ወይዘሮ  ዓይናለም አሩሳ በበኩላቸው ፤''ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነታችን ምልክት ነው'' ብለዋል።

''ሰንደቅ ዓላማን ማክበር ሀገርን ማክበር ነው'' ያሉት ወይዘሮ ዓይናለም፤ ሁሉም ዜጋ ከሙስናና አድሎአዊነት አሰራር በጸዳ መልኩ በየተሰማራንበት የሥራ መስክ የድርሻውን በመወጣት ለሀገሩ ያለውን ክብር በተግባር ሊያሳይ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የህወሓት የሽብር ቡድን በፈጸመው ወረራ  ያወደመውን ሀብትና ንብረት መልሶ ለማቋቋም  ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የነጻነት ተምሳሌት ሆኖ የቆየውን የሰንደቅ ዓላማ ክብር ማስቀጠል የትውልዱ አደራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ሰራተኛ ወይዘሪት ስመኝ ተረፈ ናቸው።  

ትውልዱ አደራውን ለመወጣት ከቃል ባለፈ በተሰማራበት የስራ መሰክ ስኬታማ ሆኖ በተግባር ሊያሳይ እንደሚገባ ጠቁመዋል።  

በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የሴክተር መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች ተገኝተዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ ''በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ'' በሚል መሪ ሀሳብ   በሀገር አቀፍ ደረጃ  ተከብሮ ውሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም