ለመኸሩ የእርሻ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ እንዲቀርብላቸው አርሶ አደሮች ጠየቁ

65
አክሱም ግንቦት 8/2010 ለመኸሩ እርሻ በግብአትነት የሚያስፈልጋቸው ማዳበሪያና  ምርጥ ዘር  በወቅቱ እንዲቀርብላቸው በትግራይ ማከላዊ ዞን  አርሶ አደሮች ጠየቁ፡፡ ለምርት ዘመኑ የሚያውል ግብአት ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ የማጓጓዝ ስራ መጀመሩን  የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡ በዞኑ የላዕላይ ማይጨው ወረዳ  የጤፍና ስንዴ ልማት ኩታ ገጠም ተብሎ ተለይቷ፡፡ በወረዳው የመደጎ ቀበሌ ገበሬ ማህበር  አርሶ አደር ተከስተ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንዳሉት  ለመኸሩ የእርሻ ወቅት መሬታቸውን አለስልሰው ዝናብ እየጠበቁ ነው፡፡ ግማሽ ሄክታር  የእርሻ መሬታቸው  ጤፍና ስንዴን በኩታ ገጠም ለማልማት  አመቺ እንደሆነ በግብርና ባለሙያዎች መለየቱን ተናግረዋል፡፡ የመሬታቸውን ምርታማነት ለማሳደግ  የሚያግዛቸውን ሰልጠና እንዳገኙ አርሶ አደሩ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ለእርሻ መሬታቸው የሚያስፈልገው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እስካሁን  እንዳልቀረበላቸውና በዚህም ስጋት እንዳደረባቸው አመልክተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ ባለመቅረቡ በእርሻ ስራቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰው ይህ እንዳይደገም ግብአቱ ከወዲሁ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቅመው በመስመር መዝራት ምርታማነትን እንደሚጨምር ባለፈው ዓመት በተግባር ማረጋገጣቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር  ጉዕሽ መለስ ናቸው፡፡ በቅርቡም  ለአምስት ቀናት ስልጠና እንደተሰጣቸው ጠቁመው  ሆኖም ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልጋቸው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንደዘገየባቸው ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደር ካሕሳይ ወልደኃይማኖት በበኩላቸው አዳዲስ የግብርና አሰራር በመከተላቸው  የተሻለ ምርት  ማግኘት እንደሚችሉ ካለፈው ተሞክሯቸው ማወቃቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግስት የግብአት አቅርቦት ዝናብ ከመጀመሩ በፊት  እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡ በዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የግብርና ስራ አስተባባሪ አቶ ተክለጊዮርግስ አሰፋ እንደገለጹት  በ2010/11 የምርት  ዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዝ ስልጠና ለአርሶ አደሮች ተሰጥቷል፡፡ ለመኸር እርሻ ወቅት የሚያስፈልግ 139 ሺህ 500 ኩንታል ማዳበሪያና 31 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማድረስ  የማጓጓዝ ስራ መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡ ግብአቱ ዝናብ ከመጀመሩ በፊት በአርሶ አደሮች እጅ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በምርት ዘመኑ በዞኑ 192 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል ለመሸፈን  ዝግጅት መደረጉንም አስተባባሪው አመልክተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም