ባለፉት ሁለት ቀናት በደረሱ የጎርፍና እሳት አደጋዎች የሞት እና የንብረት ውድመት ተከስቷል

82
አዲስ አበባ ነሀሴ 11/2010 በአዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ቀናት በደረሱ የጎርፍና እሳት አደጋዎች የሞት እና የንብረት ውድመት መከሰቱን የከተማው እሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለስልጣን አስታወቀ። አደጋዎቹን ለመከላከል በተደረገው ርብርብ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትን ከጥፋት ማዳን መቻሉንም ገልጿል። የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ስለሺ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፉት ሁለት ቀናት አዲስ አበባ ውስጥ አራት ቦታዎች የጎርፍ አደጋ ተከስቷል፤ በዚህም ሁለት ሰዎች ሞተዋል። ሰዎቹ የሞቱት ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 10 ቀን 2010 ዓም ንጋት 11 ሰዓት ላይ ሐያት ጨፌ መድሐኒያለም ፀበል ተጠምቀው አስፓልት በመሸገር ላይ ሳሉ ደራሽ ጎርፍ ወስዷቸው ነው። የባለስልጣኑ የአደጋ ባለሙያዎች ባደረጉት አሰሳ ህይወታቸው ካለፉት ሰዎች የአንዱ አስክሬን ተገኝቶ ለቤተሰቡ እንደተሰጠና ሌላኛው አስክሬን ግን እስካሁን እንዳልተገኘ ተናግረዋል። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶሰት ሰሚት ብሔራዊ እድር ቤት አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ላይ ትናንት በደረሰ የጎርፍ አደጋ 50 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል። በዚሁ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ፅህፈት ቤት ጀርባ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ላይ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ደግሞ 200 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ጠፍቷል። በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት ቄራ ጀርባ በደረሰ የጎርፍ አደጋም 350 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል። በተመሳሳይ በዛው አቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ሰርጤ ማርያም በሚባል አካባቢ ከተከሰተው ጎርፍ 500 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት መታደግ መቻሉን አመልክተዋል። እንዲሁም ከትናንት በስቲያ በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 11 በተለምዶ ሶርአምባ ኢንዱስትሪ በሚባል አካባቢ በደረሰ የእሳት አደጋ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ጠፍቷል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባደረገው ርብርብ 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትን ከቃጠሎው  ማትረፍ መቻሉንም ጠቅሰዋል። እሳቱን ለማጥፋት በተደረገው ጥረት አንድ የአካባቢው ነዋሪና ሶስት የእሳት አደጋ ሰራተኞች መካከለኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተመሳሳይ ከትናንት በስቲያ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ናይጄሪያ ኤምባሲ አካባቢ በመኖሪያ ቤት ውስጥ የእንጀራ ምጣድ ተለኩሶ ሳይጠፋ በመረሳቱ ምክንያት በደረሰ የእሳት አደጋ ሰባት ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ጠፍቷል። የአዲስ አበባ እሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለስልጣን ባለሙያዎች ከባድና ቀላል የአደጋ መኪናዎችን በመጠቀም አደጋ የመከላከል ስራ ማከናወናቸውንና በእሳት አደጋውም በብዙ ሺህ ሊትር የሚቆጠር ውሃ በመጠቀም እሳቱን የማጥፋት ተግባር መከናወኑን አስረድተዋል። ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከባድ ዝናብ ስለሚጠበቅ ህብረተሰቡ አስፈላጊ ቅድመ-ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ባለስልጣኑ አሳስቧል። በየአካባቢው የሚገኙ የተደፈኑ የማፋሰሻ ቱቦዎች በመጥረግ የሚፈሰውን የውሃ መጠን በቱቦ ውስጥ የማሳለፍ ተግባር ማከናወን እንዳለባቸው አስገንዝቧል። ከእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ በባለስልጣኑ የሚተላለፉ የቅድመ ጥንቃቄ መልዕክቶችን በተገቢው መልኩ መተግበር አለበትም ብለዋል። ነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓ.ም የሚከበረው የደብረ ታቦር በዓልን የሚያከብሩ ሰዎች ችቦ ሲለኩሱ ከኤሌክትሪክ ገመድ አርቀው መሆን እንደሚገባና የእሳት ቃጠሎ እንዳይከሰት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ህብረተሰቡ አደጋ ሲከሰት በስልክ ቁጥር 0111555300/ 0111568601 ወይም በነፃ የስልክ መስመር 939 ደውለው ማሳወቅ ይችላል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም